Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ እንድንሆን ያደረገ ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው – አለሙ ስሜ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል በመደመር እሳቤ ለአፍሪካና ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ እንድንሆን ያደረገ ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
 
“ዓድዋ የመደመር ተምሳሌታዊ አርማ” በሚል መሪ ሃሳብ ኢዜአ ያዘጋጀው የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ነው።
 
በፓናል ውይይቱ ንግግር ያደረጉት አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ “የዓድዋን ድል ስናከብር ጀግኖች አባቶችና እናቶች የፈፀሙትን ታላቅ ገድል በመዘከር ነው” ብለዋል።
 
የዓድዋ ድል መላ ኢትዮጵያውያን በህብርና በመደመር ለሀገራቸው ክብር ገድል የፈጸሙበት ተምሳሌታዊ ድል መሆኑንም ገልጸዋል።
 
“ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት በአንድነት ቆመው የማይቻል የሚመስለውን ኃይል በፅናት ታግለው በማሸነፍ የጀግንነት ገድል ፈፅመዋል” ብለዋል።
 
የዓድዋ ድል በአንድነት የተገኘ የድል ብስራት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ የዚህ ዘመን የመደመር ተምሳሌት ሆነን ሁላችንም ድህነትን ለማሸነፍ በጋራ መቆም አለብን ነው ያሉት።
 
የዓድዋ ድል ከሀገር አልፎ ለዓለም ጥቁር ህዝቦች ሁሉ የነፃነት ፋና ወጊ መሆን የቻልንበት ደማቅ የታሪክ አሻራችን ነው ሲሉም ገልጸዋል።
 
የዓድዋ ድል በመደመር የተገኘ ገድልና የዚህ ዘመን የመደመር ተምሳሌት መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ልዩነትን ወደ ጎን በመተው በጋራ ለሀገር አንድነት፣ ክብርና ልዕልና መሰለፍን የሚያስተምር እንደሆነ አንስተዋል።
 
የአሁኑ ትውልድ ከውስጥና ከውጭ በነጠላ ትርክት፣ በድህነትና ጦርነት የሚፈታተኑትን ተግዳሮቶች በአልበገር ባይነት ማሸነፍ እንዲችል ከአድዋ መማር አለበት ሲሉም ተናግረዋል።
 
ከፍታችንን ማፅናት የሚያስችሉ ተምሳሌቶችን በመውሰድ ውስጣዊ አንድነትን ከሚሸረሽሩ ጉዳዮች በመራቅ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
የዚህ ዘመን ዓድዋ ድህነትን ማሸነፍ፣ አብሮነትን ማፅናት፣ በሀሳብ ልዕልና ሀገርን መገንባት ሊሆን ይገባልም ነው ያሉት።
 
ከቅድመ አያቶቻችን የወረስነውን ታሪክ በዚህ ዘመንም ለመድገም ቴክኖሎጂን መታጠቅ፣ ጠንክሮ መስራት፣ ሌብነትን መታገልና አሰባሳቢ ትርክቶችን መገንባት ይገባል ብለዋል።
 
ኢትዮጵያውያን የጸረ-ድህነት፣ የህብረ ብሔራዊነትና የመከባበር አርበኛ እንሁን ሲሉም መልእክት ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
 
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.