Fana: At a Speed of Life!

ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ምንጩን ደብቆ ለሌሎች ግለሰቦች አስተላልፏል የተባለው ተከሳሽ በ13 ዓመት እስራት ተቀጣ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባንክ ደንበኞች ሂሳብ ተቀንሶ ገቢ የተደረገለትን ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ምንጩን ደብቆ ለሌሎች ግለሰቦች አስተላልፏል የተባለው ተከሳሽ በ13 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

የቅጣት ውሳኔውን የወሰነው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ወንጀል ችሎት ነው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ጌትነት አማረ በተባለው ተከሳሽ ላይ የሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 (ለ) እና ንዑስ ቁጥር 2 የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ እና በህገወጥ መንገድ የተገኘ ንብረትን ወይም ገንዘብን ምንጩን በመደበቅ ህጋዊ አድርጎ ማቅረብ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ) ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል የሚል ክስ አቅርቦበት ነበር።

በዚህ ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው፤ በዚሁ መዝገብ ቀደም ብሎ ጉዳያቸው ታይቶ ቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሞጣ ቀራንዮ ቅርጫፍ የባንኩ ሰራተኞች በነበሩ ሁለት ግለሰቦች አማካኝነት በርሔ ወልዴና ሸዊት አለማየሁ ከተባሉ የባንኩ ደንበኞች ፍቃድ ውጪ የአሰራርና መመሪያን በመተላለፍ በተለያዩ ቀናቶች 10 ሚሊየን 400 ሺህ ብር በመቀነስና በማጽደቅ ተሳትፎ በጥቅምት 26 ቀን በ2015 ዓ.ም በአዳማ ዲስትሪክት ሃዩ ቅርጫፍ በሀሰተኛ ማንነት በሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በተከሳሹ ስም በተከፈተ ሂሳብ ገቢ እንዲሆን መደረጉ ተጠቅሷል።

ተከሳሹ ደግሞ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም ከለሚ ኩራ ክ/ከ ወረዳ 8 በሀሰተኛ ማንነት ባወጣው ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ዲስትሪክት ሃዩ ቅርጫፍ በከፈተው ሂሳብ ውስጥ ገቢ የተደረገለትን 10 ሚሊየን 400 ሺህ ብር ወደ ተለያዩ ግለሰቦች ሂሳብ ማስተላለፉ በክሱ ላይ ተመላክቷል።

ተከሳሹ በቀረበበት ክስ ዝርዝር ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቧል።

የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻሉ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ፍርድ ቤቱ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 3 መሰረት የወንጀል አፈጻጸምና የደረሰውን ጉዳት ከግንዛቤ በማስገባት፣ ተከሳሹ ከለሚ ኩራ ክ/ከ ወረዳ 8 በሀሰተኛ ማንነት የነዋሪነት መታወቂያ በመውሰድ በአዳማ ሃዩ ቅርጫፍ የባንክ ሂሳብ በመክፈት 10 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር ገቢ የተደረገለትና ገንዘቡን ወደተለያዩ ግለሰቦች ያስተላለፈ መሆኑን በመገንዘብ የወንጀል ደረጃውን መካከለኛ የወንጀል ደረጃ በመመደብ ተከሳሹ ያቀረበው የተለያዩ የቅጣት ማቅለያ አስተያየቶች በመያዝ ከሌላ የወንጀል ድርጊት እንዲቆጠብ ለማስተማር በሚል በሁለቱም ክስ በ13 ዓመት ጽኑ እስራት እና በዕርከን 8 መሰረት በ20 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ከታህሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ታሳቢ በማድረግ የተወሰነበትን የእስራት ቅጣት እንዲያስፈጽም ታዟል።

ተከሳሹ የተጣለበትን የገንዘብ ቅጣት ለመንግስት ገቢ እንዲያደርግ የፍትህ ሚኒስቴር ተከታትሎ እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.