Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ከ250 ሺህ በላይ ሰዎች እንደጎበኙት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይ ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ ዜጎች መጎብኘቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ገልጸዋል።

አምባሳደር ብርቱካን አያኖ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ሳምንት አውደ ርዕይን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ ለ48 ቀናት የቆየው አውደ ርዕይ ከ250 ሺህ በላይ በሆኑ ሰዎች መጎብኘቱን ጠቁመዋል።

አውደ ርዕዩ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸው ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማሳየት የተቻለበት መሆኑንም ተናግረው፤ ያለፉትን 116 ዓመታት ጉዞ ማስቃኘትና ኢትዮጵያ በሁለትዮሽ እና በባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ያሳረፈቻቸውን አሻራ እንዳሳየ ገልጸዋል።

ዲፕሎማሲው አሁን ያለበት ደረጃ እና ቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በተመለከተ አቅጣጫ የሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ ስራዎችን ሰንዶ ማስቀመጥ የተቻለበት እንደሆነም ነው የተናገሩት።

የዲፕሎማሲ ሳምንቱ የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት እና ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በተመለከተ ከፍተኛ ግንዛቤ በመፍጠር መጠናቀቁን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የዲፕሎማሲ ሳምንትን ከአዲስ አበባ እና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ ጎብኝዎች፣ አዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ አምባሳደሮች፣ ዲፕሎማቶች ቤተሰቦቻቸው እና የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች እና ሠራተኞች መጎብኘታቸው ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.