Fana: At a Speed of Life!

የባንክ አሰራር ሥርዓትን ለማስተካከል በሚል የግለሰቦችን ሚስጢር ቁጥር በመውሰድ ገንዘብ ያጭበረበረው ተከሳሽ በጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባንክ አሰራር ሥርዓትን ለማስተካከል በሚል በማታለል የግለሰቦችን ሚስጢር ቁጥር በመውሰድ ገንዘብ ያጭበረበረው ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ልዩ ልዩ ወንጀል ችሎት በተከሳሹ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮ ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ሜጋ ማንዴላ የተባለ ተከሳሽን በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

የፍትሕ ሚኒስቴር የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ በተከሳሹ ላይ ሚያዚያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በኮምፒዩተር አማካይነት የሚፈጸሙ የወንጀል ጉዳዮችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 958/2008 አንቀጽ 10 ንዑስ ቁጥር 1 ስር የተመላከተውን ድንጋጌ ተላልፏል በማለት በተመሳሳይ ድንጋጌ 6 ክሶችን አቅርቦበት ነበር።

በቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ ተከሳሹ በአዲስ አበባ ከተማ በ2015 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት ለተለያዩ 6 ግለሰቦች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደተደወለ በማስመሰልና የንግድ ባንክ የአሰራር ሥርዓት በማስተካከል ሥራ ላይ እንደሆነ በመግለጽ የግለሰቦችን የሚስጢር ቁጥር እንዲነግሩት በማድረግ ከ370 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ ማጭበርበሩ ተመላክቷል።

ተከሳሹ በዚህ መልኩ የቀረበበት ክስ ዝርዝር እንዲደርሰው እና በችሎት በንባብ እንዲሰማ ከተደረገ በኋላ ግለሰቡ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምኩም ሲል ተከራክሯል፡፡

የእምነት ክህደት ቃሉን መስጠቱን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የሰነድ ማስረጃ እና የሰው የምስክር ቃል ለችሎቱ አሰምቷል።

ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃዎችን መርምሮ ተከሳሹ እንዲከላከል ብይን የሰጠ ቢሆንም ተከሳሹ ግን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን መከላከል ባለመቻሉ በተከሰሰበት ድንጋጌ የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎበታል።

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየቶችን በመያዝ ተከሳሹን በ6 ዓመት ከ6 ወራት ጽኑ እስራት እና በ6 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.