Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም የተሟላ ለማድረግ ሕዝቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም የተሟላ ለማድረግ በሚደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ የአማራ ክልል ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጎን እንዲቆም ጥሪ ቀረበ፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ዛሬ ባወጣው መግለጫ÷ በክልሉ ሕግ የማስከበር ዘመቻው በተሟላ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ሕግ የማስከበር ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጾ÷ የክልሉ ሕዝብም ከመከላከያ ሰራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጎን በመቆም ለሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል ብሏል፡፡

የክልሉ መንግሥት መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

ሕግ የማስከበር ዘመቻው በተሟላ ሁኔታ እየተከናወነ ነው።

በባህርዳር ዙሪያ የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ የፀጥታ ኃይል በጋራ ሰርጎ የገባውን ጽንፈኛ ቡድን በየቤቱ የማሠስና የማፅዳት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። እየሠራም ይገኛል።

ይሁን እንጅ የጸጥታ ኃይላችን እርምጃ መቋቋም ያቃታቸው ጽንፈኞች ራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉትን የነፍስ አድን ተኩስ እያጠቁ እንደሆነ አድርገው በሚታወቀው የውጭና የውስጥ ጽንፈኛ ሚዲያዎች እያስነገሩ ይገኛሉ።

ሰሞኑን በጎጃም እና በሌሎች አንዳንድ ቦታዎች ላይ እየተወሰደባቸው ያለውን እርምጃም እንዲሁ ማጥቃት እያደረጉ እንደሆነ ከውጭ ላለው ጽንፈኛ አጋሮቻቸው የሐሰት ፕሮፓጋንዳቸውን ሲነዙ ይስተዋላል። ይህ ፍጹም ከእውነት የራቀ መረጃ ሲሆን የምንጊዜም ማደናገሪያቸው ነዉ።

በአሁኑ ሠዓት ሙሉ በሙሉ ባህርዳር ከተማና አካባቢው ከጽንፈኛ ቡድኑ ጸድተዋል። እነዚህ ጽንፈኛ ቡድኖች የጸጥታ ኃይሉን ጥምረት መቋቋም አቅቷቸው ሙትና ቁስለኛ ሁነው የያዙትን መሳሪያ ሳይቀር እያንጠባጠቡ ሸሽተዋል።

ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እና የክልላችን የጸጥታ ኃይልም ሕግ የማስከበር ሥራውን በተሟላ ሁኔታ እየተገበረ ይገኛል።

በቀጣይም እየሸሹ እና እየተደበቁ ያሉትን ጽንፈኛ ኃይሎች በያሉበት እያሠሠ ከተደበቁበት ጉሬ እያወጣ የክልላችን ሰላም ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ በጥሩ ወኔ እና ቁመና ላይ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

በመሆኑም መላ የክልላችን ሕዝብ አሁን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም የተሟላ ለማድረግ ለሚደረገው ሕግ የማስከበር ዘመቻ ከጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን እና ከክልላችን የጸጥታ ኃይል ጎን በመቆም ለሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.