Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል ልዩነቶችን በመሻገር ሀገርን የማፅናት ተምሳሌት ነው – አቶ እንዳሻው ጣሰው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል ልዩነቶችን በመሻገር ሀገርን የማፅናት ተምሳሌት ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻዉ ጣሰዉ ተናገሩ፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ 128ኛውን የዓደዋ ድል በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፤ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር፣ የሀገር ፍቅርንና የአንድነትን እሴቶችን ሸማ የሚያጎናጽፍ ነው ብለዋል።

በዓሉን ስናከብር ሉዓላዊነትን፣ ብሔራዊ ጥቅምን እና ብሔራዊ  ክብርን በጋራ የማፅኛ እሴቶችን ከቀደምት አባቶችና እናቶች ምግባር  እየተማማርን መሆን ይኖርበታል  ሲሉ ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል ልዩነቶችን በመሻገር ሀገርን የማፅናት አስተምህሮ ነው በማለት ጠቅሰው፤ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመሻገር ሁሉም ዜጋ  ኢትዮጵያን ለማበልፀግ ወደፊት መራመድ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗ ኢትዮጵያዉያን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለብሔራዊ ጥቅሟና ክብሯ ዘላቂነት በጋራ ከመሰለፍ እንዳልገታቸዉ የዓድዋ ድል ህያዉ ምስክር ነዉ ብለዋል።

በመሆኑም የዓድዋ ድል እሴቶችን በመሰነቅ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መትጋት እንዲሁም ለሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነት እሴት ማበብ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

የቀደምት አባቶችና እናቶች የዓድዋ ድል ዐሻራ የዛሬዉን ሀገራዊ ፈተናዎች በማሸነፍ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ለዉጥ እዉን ለማድረግ የብርታትና የፅናት ምንጭ አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ መጠቆማቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.