Fana: At a Speed of Life!

ዓድዋ በአጥንት ብዕር የተጻፈ ቼክ ነው፤ እየመነዘርን መጠቀም የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው – ምክትል ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓድዋ በአጥንት ብዕር የተጻፈ ቼክ ነው፤ እየመነዘርን መጠቀም የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው÷ ዐድዋ ሀብት ነው፤ አባቶቻችን ያቆዩልን ሀብት፤ በደም ቀለም፣ በአጥንት ብዕር የተጻፈ ቼክ ነው፤ እየመነዘርን መጠቀም የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ሆኖ ዘምቶ፣ አንድ ሆኖ ተዋግቶ፣ አንድ ሆኖ ድል አድርጓል ያሉት አቶ ተመስገን፤  ኅብረ ብሔራዊነቱ በጥበብ፣ በዐቅምና በስልት ልዩ ልዩ መንገዶችን እንዲጠቀም ረድቶታል ሲሉ ገልፀዋል።

አንድነቱ ደግሞ ለአንድ ዓላማ ዘምቶ፣ ለአንድ ዓላም ተዋግቶ፣ አንድ የጋራ ድል እንዲያገኝ አድርጎታል ሲሉ ተናግረዋል።

ዓድዋ የኢትዮጵያ ልክም መልክም ነው፤ ልክነቱ ማናቸውንም ችግሮቻችንን አንድ ሆነን ማሸነፍ እንደምንችል ማሳየቱ ነው፤ መልክነቱ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚገባ መግለጡ ነው ብለዋል፡፡

ይህንን ልክና መልክ ጠብቀንና ከፍ አድርገን በመጠቀም ኢትዮጵያን ከአድዋ ከፍታ በላይ እንደምናደርሳት እምነቴ ነው ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.