Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በጋራ መታገል እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ ነው – አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝን በጋራ መታገል እንደሚገባ ትምህርት የሰጠ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ተናገሩ።

አምባሳደሩ፤ የዓድዋ ድል በዓለም ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ውጤት ነው ብለዋል።

ድሉ የቅኝ ግዛት አስተሳሰባቸውን በሌሎች ላይ ለመጫን በሚፈልጉ አካላት ላይ የተገኘ ለአንድ የጋራ ግብ የተሰባሰቡ ኢትዮጵያዊያን ባካሄዱት ትግል የተገኘ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዓድዋ ጀግኞች መታሰቢያ እንዲገነባ ውሳኔ ማሳለፋቸውና በተግባርም እውን እንዲሆን ማድረጋቸው ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ድሉን ለመዘከር የተገነባው የዓድዋ ድል መታሰቢያም የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው አፍሪካውያን ጀግኖች መታሰቢያ መሆኑን ተናግረዋል።

መታሰቢያው ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የጸረ ቅኝ ግዛት ትግል ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ያሉት አምባሳደሩ÷ መታሰቢያው አዲሱን የቅኝ ግዛት አካሄድ መታገል እንደሚያስፈልግ የሚያስገነዘብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም የዓድዋ ድል 128ኛ ዓመት ሲከበርም ከአሁናዊ ዓለም አቀፍ አውድ አንጻር ትምህርት በመውሰድ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.