Fana: At a Speed of Life!

128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ታሪኩን በሚዘክር ቦታ መከበሩ ልዩ እንደሚያደርገው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዘንድሮው የዓድዋ ድል በዓል ታሪኩን በተግባር በሚዘክር ቦታ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች ዓርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ ተናገሩ፡፡

 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የጥቁር ሕዝቦች ድል በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡

ልጅ ዳንኤል ጆቴም በበዓሉ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት÷ የዘንድሮው የዓደዋ ድል በዓል ጀግኖች አባቶቻቸን ያደረጉትን ተጋድሎ በሚዘክረው የዓድዋ ድል መታሰቢያ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉ በንግግርና በስብሰባ ብቻ ሳይሆን ታሪኩን በሚዘክሩ ተሻጋሪ ሥራዎች ጭምር በመከበሩም መደሰታቸውን ተናግርዋል።

ይህን ሐሳብ አመንጭተውና በአጭር ጊዜ ወደ ተግባር ቀይረው ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ለሠሩ አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል።

የመታሰቢያው መገንባት  ወጣቱ ትውልድ ታሪኩን በሚገባ እንዲያጠናና የዓርበኝነት መንፈሱ እንዲያድግ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ድሉ አፍሪካን የመቀራመት አካሄድ ያከሸፈና ሌሎችን ለትግል ያነሳሳ የይቻላል መንፈስ የፈጠረ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በአንድ ልብ በመነሳት የዓለምን ታሪክና ትርክት የቀየሩበት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ድሉ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ መሆኑን ጠቅሰው በጥቁሮች ላይ ይደርስ የነበረውን ግፍ ለማስቀረት የብዙዎችን ዐይን የከፈተ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ትልቅ ድል የሚዘክር መታሰቢያ መንግስት በአዲስ አበባ መገንባቱ ትልቅ ክብርና ምስጋና የሚያሰጠው ነው ብለዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.