Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ ሠራዊት የዓድዋ ጀግኖችን ተጋድሎ ውርሱ አድርጎ ለሀገሩ በኩራት ዘብ ይቆማል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሠራዊት የዓድዋ ጀግኖችን ተጋድሎ ውርሱ አድርጎ ለሀገሩ በኩራት ዘብ እንደሚቆም የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

‹‹ዓድዋ የመላው ጥቁር ሕዝቦች ኩራት›› በሚል መሪ ሐሳብ 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ፒያሳ በሚገኘው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተከብሯል፡፡

በዚሁ ወቅት ንግግር ያደረጉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ የዓድዋ ድል ደማቅ ታሪክ የተጻፈበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲልም ለትውስታ ብቻ ይከበር እንደነበር አስታውሰው÷ ዘንድሮ ግን ድሉን የሚመጥን መታሰቢያ በዚህ ትውልድ ተገንብቷል ብለዋል፡፡
የጦር መሪዎችን ጨምሮ ብሔር ብሔረሰቦችም በመታሰቢያው መካተታቸውን አድንቀዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት የዓድዋ ጀግኖችን ሥራ ውርሱ አድርጎ ለሀገሩ በኩራት ዘብ እንደሚቆምም አረጋግጠዋል፡፡
አንድነትን ከዓድዋ መማር ይገባል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ÷ አንድነትን ለመሸርሸር የሚጥሩ ፀረ-ሠላም ኃሎችን ሕዝቡ መታገል እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
እንደ መከላከያም የሚጠበቅብንን በውጤት የታጀበ ሥራ እያከናወንን ነውም ብለዋል፡፡
ሀገራችን ጠንካራ የመከላከያ ኃይል እንዳላትም ለኢትዮጵያውያን ማረጋገጥ እፈልጋለሁ ነው ያሉት በንግግራቸው፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ከሀገራችን አልፎ ለሌሎች ሀገራትም ኩራትና መከታ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህንንም የወደቀላቸው ይመሰክራሉ ሲሉም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ምን ጊዜም አሸናፊ ናት፤ ዛሬም የዓድዋ ጀግኖች ልጆች መሆናችንን እያስመሰከርን እንቀጥላለን ሲሉም አንስተዋል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.