Fana: At a Speed of Life!

የዓድዋ ድል የዓላማ አንድነት ውጤት ነው – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓድዋ ድል የዓላማ አንድነትና የጽናት ውጤት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ፡፡

128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በተመለከተ አገልግሎቱ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫውም÷ የዓድዋ ድል የዓላማ አንድነትና የጽናት ውጤት መሆኑን አስገንዝቧል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

የዓድዋ ድል የዓላማ አንድነትና የጽናት ውጤት ነው!

ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድም ጊዜ የሌላውን ፍለጋ ጥቃትና ወረራ ፈፅማ አታውቅም፡፡ በአንፃሩ ጠላቶችዋ በተለያዩ ዘመናት በተደጋጋሚ ከሩቅና ከቅርብ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ ፈፅሟል፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያዊያን ተሸንፈው እጅ የሰጡበት ወቅት የለም፡፡ ሁሉንም ወራሪዎች ድል አድርገው አንገት በማስደፋት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር አስጠብቋል፡፡

ከእነዚህ የወረራ ታሪክና የድል አድራጊነታችን የሁል ጊዜ ኩራታችን የሆነው ውቅያኖስን አቋርጠው ኢትዮጵያ ላይ ወረራ በመፈፀም ሉዓላዊነታችንን ለመጋፋት የተንቀሳቀሱ የቅኝ ገዢ ሕልምና ምኞት ያከሰመው የዓድዋ ድል ነው። ኢትዮጵያውያን ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ የተቃጣባቸዉን የኢጣሊያን ወረራ በመመከት ዓለምን ጉድ ያሰኘ ታላቅ ጀብዱ በዓድዋ ተራሮች ላይ የፈጸሙት የዛሬ 128 ዓመት፣ በየካቲት 23/1888 ዓ.ም ነበር።

የዓድዋ ድል የመላ ጥቁር ሕዝቦችን ነጻነት ያበሰረ የክፍለ ዘመኑ ታላቅ ድል ነበር። ውርደትና ሽንፈትን የተከናነበው የኢጣሊያን ጦር ሞትና ምርኮኛ ሆኖ በዓድዋ ተራሮች ላይ ቀርቷል። በዚህም ሮምን ጨምሮ የዓድዋ የድል ችቦ በመላው ዓለም ላይ ተቀጣጥሏል። ጥቁሮች ነጭን ማሸነፍ እንደሚችሉ በተግባር ያስመሰከሩበት የተጋድሎ ውጤትም ሆኖ በታሪክ ተመዘገበ። በመሆኑም የዓድዋ ድል የአይበገሬነት፣ የአትንኩኝ ባይነት የጋራ ኅብረት የተንፀባረቀበት በደመቀ የደም ቀለም የተጻፈ የመላው የጥቁር ሕዝቦች የትግል ታሪክ ነው።

የዓድዋ ድል በመላው ኢትዮጵያውያን ተሳትፎና ተጋድሎ የተገኘ አስተሳሳሪ ድል ነው። የብሔር፣ የቋንቋ፣ የአካባቢና የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነት ሳይገድባቸው አባቶቻችን ለጋራ ዓላማ በአንድነት መስዋዕትነት ከፍለው ነፃ ሀገር እንድንረከብ ያደረገን ድል ነው፡፡ በአንድነት በከፈሉት መስዋዕትነትና በደማቸው የተፃፈ የጋራ ድልና ታሪክ አውርሰውናል፡፡ ድሉን ሊያጎናፅፉን የቻሉት በታጠቁት ዘመናዊ መሣሪያ ወይም አደረጃጀት ሳይሆን ለጋራ ዓላማ በፅናትና በአንድነት በመሰለፋቸው ነው። በመሆኑም የዓድዋ ድል ትውልድ ሊማርበት የሚገባው የዓላማ አንድነትና የፅናት ውጤት ነው፡፡

የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያንም አልፈው ቅኝ ለተገዙ ሕዝቦችም የነፃነት ጮራ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ላይ ዓድዋን ስናስብ የጋራ ድልና ታሪክ መሆኑን በመገንዘብ የሚገባዉ ክብር በመስጠት በሚመጥነዉ ዓለማቀፍ ከፍታ ልክ በድምቀት ልንዘክረው ይገባል፡፡

ዘንድሮ የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር፤ የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም ተመርቆ ሥራ በጀመረበት ማግሥት ነው፡፡ የፓን አፍሪካኒዝም ምልክትነቱን የሚመጥን መታሰቢያ ሙዚዬም ተገንብቶ በአፍሪካ ኅብረት ጉባኤ ወቅት ልዩ ልዩ ጉባኤዎችን አስተናግዷል፡፡ ይህም መንግሥት የሀገር አንድነትን ለማጽናት ለጋራ ድልና ትርክት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያሳይ ነው፡፡ የዚህ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይህንን አኩሪ የድል ታሪክ ለትውልድ ከማሸጋገርም ባሻገር በዓድዋ ድል ዙሪያ ለሚደረጉ ጥናቶችና ምርምሮች የላቀ ፋይዳ ይኖረዋል።

የዓድዋ ድልን ስንዘክርና ስናከብር ልንማራቸው ከሚገቡ ቁምነገሮች አንዱ ሀገራችን በማንኛውም ወቅት የሚገጥሟትን ፈተናዎች በድልና በስኬት መወጣት እንደምትችል የዓድዋ ድል ዋነኛ ተምሳሌት መሆኑን ነው። ፈተናዎችን በድል ለማጠናቀቅ ነጠላ ትርክቶችን ወደ ጎን በመተው እንደ ዓድዋ ጀግኖች ከሰፈር አስተሳሰቦች በመላቀቅና ሀገርን በማስቀደም አንድ ላይ መቆምን ይጠይቃል፡፡ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን በድል ለማጠናቀቅና የሀገራችንን ብልፅግና እውን ለማድረግ ከዓድዋ ጀግኖች ፅናትና አንድነት መማር ያስፈልጋል፡፡

እንኳን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
የካቲት 23/2016 ዓ/ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.