Fana: At a Speed of Life!

ጠ/ሚ ዐቢይ በኬንያ እና ታንዛኒያ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በኬንያ እና ታንዛኒያ ያደረጉትን ይፋዊ ጉብኝት አጠናቀው ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ(ዶ/ር) እና ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ከቀናት በፊት ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ኬንያ ማቅናታቸው ይታወቃል፡፡

በጆሞ ኬንያታ አውሮፕላን ጣቢያ በኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን÷ በመቀጠልም ፕሬዚዳንት ሩቶ የወጣቶችን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተሳትፎ የሚያሳይ የአይሲቲ ፓርክ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)አስጎብኝተዋል።

ሁለቱ መሪዎች ውይይትያደረጉ ሲሆን በውይይታቸውም ÷የሁለቱን ሀገራት ጥልቅ እና ታሪካዊ ግንኙነት ብሎም ኢኮኖሚያዊ ትስስር አውስተው ይህንኑ በቁርጠኝነት ማጠናከር እንደሚገባ ተስማምተዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)በኡሁሩ መስክ የአበባ ጉንጉን የማስቀመጥ ሥነ-ሥርዓትም አካሂደዋል።

ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር) በኬንያ ቆይታቸው ከፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር በመሆን በኬንያ ሱስዋ ናሮክ ወረዳ የሚገኘውን እና ከኢትዮጰያ በኩል ከወላይታ ሶዶ የ500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ ኃይል መለወጫ ጣቢያ መስመር ማብቂያ የሆነውን የኬትራኮ ኮንቨርተር ስቴሽንን ጎብኝተዋል።

በመቀጠል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኬንያ ቆይታቸውን አጠናቅቀው ለይፋዊ የስራ ጉብኝት ወደ ታንዛኒያ ያቀኑ ሲሆን ÷በፕሬዚዳንት ሳሚያ ሱሉህ ለይፋዊ ውይይት ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

ውይይታቸው የሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ መጠነ ርዕይ ባላቸው ሰፋፊ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠነ ሲሆን÷ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ለማስፋት ፅኑ አቋም በመያዝ የተከናወነም ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነበራቸው ቆይታ ለታንዛኒያው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ ሀሰን ምዊኒ በተዘጋጀው የመታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይም ሀዘናቸውን ለመግለጽ በስነ- ስርዓቱ ተገኝተዋል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.