Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የት/ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ የት/ቤቶችን ደረጃ የማሻሻልና ግብዓት የማሟላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) እንደገለፁት÷በክልሉ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻልና ግብዓት በማሟላት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ120 በላይ ትምህርት ቤቶችን በአዲስ በመገንባትና በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ በማቋቋም ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉን ተናግረዋል።

“ደረጃቸውን ጠብቀው የተገነቡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለአገልግሎት መብቃታቸው ለትምህርት ጥራት መረጋገጥ ከፍተኛ ሚና አላቸው” ብለዋል።

በተጨማሪም ከ8 ሚሊየን በላይ የ1ኛ ደረጃ የመማሪያ መጽሐፍትና ከ82 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ከ44 ሺህ በላይ የተማሪ መቀመጫ ዴስኮችና ሌሎች ግብዓቶች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።

በትምህርት ሚኒስቴር ታትመው የተዘጋጁ መጽሐፍትም በክልሉ እየተሰራጩ እንደሆነ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በጅምር ላይ ያሉ የትምህርት ቤቶች ግንባታ ማጠናቀቅና ተጨማሪ ግብዓት የማሟላት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም የቢሮ ሃላፊዋ አስታውቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.