Fana: At a Speed of Life!

የልብ ህመም በምን ምክንያት ይከሰታል?

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የልብ ህመም የልብን ስራ የሚያስተጓጉሉ የተለያዩ የልብና የደም ዝውውር ችግሮችን የሚያጠቃልልና ከባድ ከሚባሉት የህመም አይነቶች የሚመደብ ነው።

የልብ የጤና ችግሮች በሁለት ይከፈላሉ፤ እነርሱም፦ ከውልደት ጋር (በተፈጥሮ) የሚመጡ እና ከውልደት በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የሚመጡ የልብ በሽታዎች በመባል ይታወቃሉ።

በተፈጥሮ የሚመጣው የልብ በሽታ፡- ሕፃናት ሲወለዱ ጀምሮ አብሮ የሚመጣ ሲሆን÷ ከተወለዱ በኋላ እንደ ችግሩ ግዝፈት ወይም መጠን በተለያየ ጊዜ ላይ የበሽታውን ምልክት ሊያሳዩ ይችላሉ።

ወይም ደግሞ ምንም ምልክት ሳያሳይ ሕይወታቸውን ሊገፉ ይችላሉ።

የልብ ክፍልፋዮች አለመለያየት፣ በበቂ ሁኔታ አለመከፈት ወይም ደግሞ መከፈት የሌለበት ቦታ መከፈት … ወዘተ የመሳሰሉት ከልብ አፈጣጠር ጋር የሚመጡ የልብ የተፈጥሮ ችግሮች ናቸው።

ከውልደት በኋላ ከሚመጡ የልብ የጤና ችግሮች ውስጥ በብዛት ተሰራጭቶ የሚገኘው እድሜ እየጨመረ ሲሄድ የሚመጣ የልብ ችግር ነው።

ለዚህ የልብ ችግር ከእድሜ በተጨማሪ የአኗኗር ሁኔታ አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ነው። ሌላው በልጅነት ከጉሮሮ ቁስለት (ከቶንሲል) ጋር ተያይዞ የሚመጣ የልብ ችግር ተስፋፍቶ ይገኛል።

በመሆኑም የቶንሲል ችግር ሲያጋጥም ጉዳዩን ችላ ሳይሉ በፍጥነት ወደ ህክምና ተቋማት በመሄድ ተገቢውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ከዚህ አንጻር ጤነኛ ያልሆነ የአመጋገብና የአኗኗር ዘይቤ፣ የአልኮል መጠጥና የአደንዛዥ ዕጾች አጠቃቀም እንዲሁም ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ የሚመጡ እንደ ደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የደም የኮሌስትሮል መጨመር የመሳሰሉ ችግሮች ከውልደት በኋላ ለሚያጋጥም የልብ በሽታ የሚያጋልጡ ዋና ዋና መንስኤዎች ናቸው።

በተለይ ከውልደት በኋላ ለሚከሰተው የልብ ህመም ተጋላጭ ከሚያደርጉ የአኗኗርና የአመጋገብ ዘይቤ መራቅ እንዲሁም ከልክ በላይ አልኮል ከመጠጣት፣ አደንዛዥ ዕጽ ከመጠቀምና ሲጋራ ከማጨስ በመታቀብ፤ ቀድሞ በሽታውን ለመከላከል ጤነኛ የአመጋገብ ሥርዓት መከተል፣ የእግር መንገድ መጓዝና አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የህክምና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.