Fana: At a Speed of Life!

ከባሕር ዳር – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው መስመር በመበጠሱ ኃይል ተቋረጠ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከባሕር ዳር – ደብረታቦር – ንፋስ መውጫ – ጋሸና – አላማጣ የተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በመበጠሱ በአካባቢዎቹ ኃይል መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር ውበት አቤ እንዳሉት÷ ዛሬ ከረፋዱ 4፡30 ሠዓት ጀምሮ በንፋስ መውጫ አካባቢ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ አንደኛው ፌዝ ተበጥሷል፡፡

ይህን ተከትሎም ከንፋስ መውጫ – ጋሸና- አላማጣ – መኾኒ- መቀሌ የሚሄደው መስመር ኃይል ተቋርጣል ብለዋል፡፡

የደረሰውን ጉዳት በአፋጣኝ በመጠገን አገልግሎቱን ለመመለስ እየተሠራ ነው ማለታቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ ከደብረ ብርሃን – ሸዋሮቢት – ኮምቦልቻ የተዘረጋው መስመር በሸዋ ሮቢት ከተማ አቅራቢያ በመበጠሱ ከሸዋ ሮቢትና ከሚሴ ከተሞች በስተቀር አብዛኛዎቹ የሰሜን ምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ኃይል መቋረጡን የሪጅኑ ዳይሬክተር በድሩ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡

ከኮምቦልቻ በባቲ ኃይል ሲያገኙ የነበሩት ሠመራና የተለያዩ የአፋር ክልል ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም በወልዲያ አላማጣ መስመር ኃይል ሲያገኙ የነበሩት መቀሌን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የትግራይ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከትናንት በስቲያ ከሰዓት በኋላ የተበጠሰውን መስመር በመጠገን አገልግሎቱን ለማስቀጠል ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.