Fana: At a Speed of Life!

በአማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምና ህግ ማስከበር ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማራና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሰላምና ህግ ማስከበር ላይ ያተኮረ ውይይት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

በትናንትናው እለት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይም የሁለቱ ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ የአጎረባች ወረዳ አስተዳዳሪዎችና አመራሮች እንዲሁም የምዕራብ እዝ ከፍተኛ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በሁለቱ ክልሎች የሰላም ውይይት ላይ እንዳሉት በመተከልና አካባቢው በተፈጠረ ግጭት የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም ተከስቷል።

የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ በመረጃ ላይ ተመስርቶ በድርጊቱ የተሳተፉ ወንጀለኞችን ለመለየትና ለመቆጣጠር የተሰራ ስራ ቢኖርም አሁንም መፈታት ያለባቸው ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ተናግረዋል።

በየደረጃው የሚገኘው የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በአካባቢው የተቋቋመው የኮማንድ ፖስት አመራርን እንደ ወርቃማ እድል በመጠቀም ወንጀለኞችን በመያዝ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይገባል።

ይህም በአካባቢው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማስፈርና በአካባቢው የተሰማሩ ባለሃብቶችን ዘላቂ ደህንነት በማስጠበቅ አካባቢውን የልማት ኮሪደር ለማድረግ የጋራ ስራ የሚጠይቅ እንደሆነ አብራርተዋል።

እስካሁን ችግራቸው ያልተፈታላቸውና የጸረ ሰላም ሃይሎች እንቅስቃሴ አለባቸው ተብለው በተለዩ ሁለት ቀበሌዎችም በመነጋገር ጥምር የፀጥታ ዘመቻ በማካሄድ አካባቢውን ወደ ነበረበት ሰላም መመለስ ይገባልም ብለዋል።

ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል ከመጡት ከ49 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መካከልም በቅርቡ 14 ሺህ 650 የሚሆኑትን ወደ ነበሩበት የመመለስ ስራ መከናወኑ አበረታች መሆኑን ተጠቅሷል።

በተለይም ከአማራ ክልል ተፈናቅለው በለስ ከተማ አካባቢ የነበሩ 1 ሺህ 575 ዜጎች ወደ ጃዊ ሙሉ ለሙሉ መመለስ መቻላቸውና ለሁሉም ተፋናቃዮች የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ መጀመሩ ተገቢነት ያለው ስራ መሆኑን ገልፀዋል ።

የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሃሰን በበኩላቸው የአካባቢውን ሰላም ቀድሞ ወደ ነበረበት በመመለስ ሰላማዊ የልማት ቀጠና ለማድረግ የአማራ ክልል ድጋፍ አስፈላጊ ነው ብለዋል።

ለዚህም የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስተካከልና በቀጣይም ሌሎች ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል በየጊዜው የጋራ መድረክ በመፍጠር እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

በችግሩ ውስጥ ተሳትፈዋል የተባሉ አመራሮች፣ የፀጥታና ሌሎች አካላት ላይ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ ከመውሰድ ባሻገር መልሶ የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አሁን ላይ የኮሮና በሽታ በመከሰቱ ማወያየት ባይቻልም በቀጣይ ከህዝቡ ጋር ተከታታይ ምክክር በማካሄድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት ክልሉ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የምዕራብ እዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል መሰለ መሰረት በበኩላቸው የኮማንድ ፖስቱ ዋና ዓላማ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ሰላምና መረጋጋት ማስፈንና ተፈናቃዮችን ቀድሞ ወደ ነበሩበት መመለስ ነው።

በዚህም የመከላከያ ሰራዊቱ ከአካባቢው መስተዳድርና ከህዝቡ ጋር ተቀራርቦ በመስራቱ አሁን የሚታየው ሰላምና መረጋጋት በማምጣት የተፈናቀሉትን ወደ ነበሩበት የመመለስ ስራ እንዲከናወን አስችሏል።

በተካሄደው የተጠናከረ ስራም ለጥፋት ይውል የነበረ 80 የጦር መሳሪያ ፣ 870 ጥይትና ከ10 ሺህ 500 በላይ ዘመናዊ ቀስት በቁጥጥር ስራ መዋሉን በሪፖርቱ መመልከቱን ኢዜአ ዘግቧል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.