Fana: At a Speed of Life!

የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መጀመሩ  መንግሥት ዜጎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን ቸል እንዲሉ እንደፈቀደ ሊታሰብ አይገባም – ጠ/ሚ ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 30፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መጀመሩ  መንግሥት በምንም ዓይነት ዜጎች የጥንቃቄ እርምጃዎችን ቸል እንዲሉ እንደ ፈቀደ ወይም አቋሙን እንዳላላ ተደርጎ ሊታሰብ እንደማይባ ጠቅላይ ሚኒስት ዶክተር ዐቢይ አህመድ አሳሰቡ ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ የኮቪድ-19 ወረርሳኝ እና ሊወሰድ በሚገባው ጥንቃቄ ላይ የሚከተለውን መግለጫ አውጥተዋል።

በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በኮቪድ19 የተያዘ ሰው ከመገኘቱ አስቀድመን፣ የመከላከል ሂደቱን በበላይነት የሚመራ የሚኒስቴሮች ኮሚቴ መቋቋሙን ገልፀዋል።

በመቀጠልም ልዩ ልዩ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው ቫይረሱን የመከላከል እና ሥርጭቱን የመግታት ሥራ በበቂ ዝግጁነት እንዲከናወን እና ተመጣጣኝ መፍትሔዎችን ለመስጠት እንዲቻል ሲሠሩ ቆይተዋልም ነው ያሉት።

እነዚህ ንዑሳን ኮሚቴዎች ለይቶ መከታተያ፣ ለይቶ ማቆያ እና ለይቶ ማከሚያ ማዕከላትን በሀገር ደረጃ በማቋቋም፣ በግለሰብ ደረጃ ቫይረሱን ለመከላከል እንዲቻል ከሚረዱ ግብአቶች አንሥቶ ልዩ ልዩ የሕክምና መገልገያዎችን በመግዛት እና ድጋፍ በማፈላለግ፣ ከሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማሰባሰብ ግብአቶች የሚቀርቡበትን ሁኔታ በማመቻቸት፣ እጅግ አስከፊ ሁኔታ ቢከሠት ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚጠቀሙበትን ምግብ በማከማቸት እንዲሁም፣ የማክሮ ኢኮኖሚያዊ ደንቦችን በማውጣት እስካሁን ሥራቸውን ማከናወናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ ቢጨምር፣ ሕዝቡ ተገቢው ዝግጅት ሊኖረው እንዲችል ልዩ ልዩ ርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸውን አንስተዋል።

የቫይረሱ ሥርጭት ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥሩ ጨምሮ በኅብረተሰቡ መካከል መዛመት መጀመሩ የሚስተዋል ነው ብለዋል።

መንግሥት ባለፉት ሦስት ወራት ቫይረሱን ለመግታት እና ሥርጭቱን ለመከላከል ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱ በማስታወስ ሆኖም እያንዳንዱ ግለሰብ የቫይረሱን ሥርጭት ለመከላከል የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ እንደ ሆነ ሊስተዋል ይገባል ነው ያሉት፡፡

የዚህ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ ተከላ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩ መጀመሩ፣ መንግሥት በምንም ዓይነት ዜጎች የጥንቃቄ ርምጃዎችን ቸል እንዲሉ እንደ ፈቀደ ወይም አቋሙን እንዳላላ ተደርጎ ሊታሰብ አይገባም ብለዋል፡፡ የመከላከል እርምጃዎችን በጥብቅ መፈጸም አሁንም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማንሳት።

የተቀመጡ ቫይረሱን የመከላከል እርምጃዎች ተግባራዊ እየተደረጉ፣ ምርታማነታችንን መቀጠል እና ግባችንን ማሳካት አለብን ብለዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የአንድ ቀን ሥራ እንዳልሆነ እና መላውን ክረምት የሚከናወን ሂደት መሆኑን አስታውቀዋል።

ተግባራዊነቱም በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ የሚፈጸም እንደሆነ በመግለፅ “ስለዚህ በቤተሰብ ደረጃ ርቀታችንን እየጠበቅን የምናደርገው ችግኝ ተከላ፣ ኮቪድ-19ን ከመከላከል እርምጃ ጋር አብሮ የሚከወን ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም የፈጠራ ሥራን ለሚሠሩ እና ጠቃሚ ሐሳቦችን ለሚያመነጩ ሰዎች እንደ ዕድል ተደርጎ ሊወሰድ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ሁኔታው የኮቪድ-19 መከላከል እርምጃዎችን እየተገበርን እንዴት እና በምን መንገድ 5 ቢሊየን ችግኞችን የመትከል ዕቅዳችንን እንደምናሳካ በርካታ ሐሳቦችን እንዲያፈልቁ የሚጋብዝ ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.