Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በገጠር አካባቢዎች ለማስፋፋት መስራት አለባት – የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በገጠር አካባቢዎች ለማስፋፋት መስራት አለባት ሲል የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ገለጸ፡፡

የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ያሉበትን ተግዳሮቶች እና እድሎችን የተመለከተ ዝርዝር መረጃ አውጥቷል፡፡

በፈረንጆቹ 2020 የጀመረው የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ፥ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገትን፣ የዜጎችን ተሳትፎ እና የተሻለ የህይወት ጥራትን ለማምጣት ያለመ ነው።

አብዛኛው ወጣት የሆነውና እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር የጠቀሰው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም፥ በትምህርት ገበታ ያለፈና እያለፈ የሚገኘው 26 ሚሊየን የሚሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ክፍል ለዘርፉ ጥሩ እድል ይዞ እንደሚመጣ ገልጿል።

ኢትዮጵያ የዲጂታል ልማትን ሃይል በመጠቀም ለወጣቱ ለቀጣይ ስራ አስፈላጊ የሆነውን ክህሎት በማስታጠቅ ፈጠራውን በማጎልበት እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገትን በመላ ሀገሪቱ እንዲመራ ማድረግ ትችላለችም ብሏል።

የኢትዮጵያ ኢንተርኔት አጠቃቀም ከ36 ሚሊየን በላይ ያደገ ቢሆንም የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኘው ህዝብ ውስን መሆኑን የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም አንስቷል፡፡

ይህም ሆኖ ግን እንደ ዲጂታል መታወቂያ እና የሞባይል ክፍያ ለዳበረ ዲጂታል ስነ-ምህዳር ጠንካራ መሰረት እየጣሉ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከ40 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት የሞባይል ተጠቃሚዎች ያሉት የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሞባይል ስልክ ቁጥር ዲጂታልን የማካተት እድልን የበለጠ ያሳየ ነውም ብሏል።

በኢትዮጵያ ሁሉን ያካተተ ለውጥ ለማምጣት በመሰናክሎች እንዳሉ የገለጸው ፎረሙ፤ በገጠር አካባቢ ለሚመረቱ የሀገር ውስጥ ምርቶች እና የግብርናውን ዘርፍ ለመደገፍ የተዘጋጁ ጥቂት የኢ-ኮሜርስ ስርዓቶች ብቻ እንዳሉ በአብነት አንስቷል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል የዲጂታል ዓለምን ለመጠቀም የሚያስፈልገው ዲጂታል ክህሎት ይጎድለዋል ያለው መረጃው፥ ይህም ብዙዎች በዘርፉ ያለውን ጥቅም እንዳያገኙ ያደርጋል ብለዋል።

በከተሞች የዲጂታል አገልግሎት የተሻሻለ ቢሆንም ፥ አብዛኛው ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባቸው የገጠር አካባቢዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ውስን መሆኑ ተነስቷል።

ይህም በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ፍትሃዊ እንዳይሆን ያደርጋልም ብሏል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የሞባይል ስልክ ከፍተኛ ቁጥር ቢኖረውም ፥ የሞባይል ስልኮችን ለድምጽ ግንኙነቶች ብቻ በመጠቀም የተገደበ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትክክለኛ አቅምን ለማሳየት ኢትዮጵያ ለኢ-አስተዳደር አገልግሎቶች፣ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የተነደፉ የኢ-ኮሜርስ ስርዓቶችን እና ለዜጎች ጤና እና ትምህርት መጎልበት የሚያገለግሉ የዲጂታል መሳሪያዎች፣ ንግዶችን እና ተቋማትን ማብቃት ላይ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባትም ድርጅቱ ባወጣው መረጃ ገልጿል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎትን በተለይም በገጠር አካባቢዎች ለማስፋፋት መስራት እንዳባትም ጠቁሟል፡፡

ከሁሉም በላይ የክህሎት ስልጠናዎችን መስጠትና ስለዲጂታሉ ዓለምና አጠቃቀም ማስገንዘብ እንደሚገባ አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነዋሪዎችን ልዩ ፍላጎት የሚያሟሉ የሞባይል መተግበሪያዎችን በማዘጋጀት እና በማስተዋወቅ የሞባይል አጠቃቀም ስርዓቶችን ማስፋት እንዳለባትም ጠቁሟል።

እነዚህን ተግዳሮቶች በመፍታትም ኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞዋን በአግባቡ ማስኬድ ትችላለችም ነው ያለው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.