Fana: At a Speed of Life!

የአዲስ አበባ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ነገ ይጀመራል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 30 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ1 ሚሊየን በላይ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት የአዲስ አበባ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ነገ ይጀመራል፡፡
 
መርሀግብሩ ለአራት ወራት ይቆያል የተባለ ሲሆን ይህን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ እና የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
 
በዚህም የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በተለይም የኮሮና ቫይረስን መከላከል ላይ የሚደረጉ ጥረቶች በማገዝ ላይ የሚያተኩር ይሆናል ነው የተባለው::
 
በመርሀግብር ውስጥ «አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው» የሚል ፕሮግራም የተካተተ ሲሆን 500 አባወራዎችን ተጠቃሚ የሚሆኑ ይሆናል ተብሏል።
 
እንዲሁም በከተማዋ በቅርቡ ለተቋቋመው ከ1ሺህ200 በላይ የምግብ ባንኮች ለ480 ሺህ አባወራዎች የሚበቃ ምግብ የማሰባሰብ ስራ በበጎ ፈቃደኞቹ ይከናወናል፡፡
 
በ”ስጦታ ለአዲስ አበባዬ” መርሀግብር ደግሞ 100ሺህ የትምህርት መሳሪያዎች፣ 50ሺህ አልባሳት እና 100ሺህ የተለያዩ ቁሳቁሶች የማሰባሰብ ስራ እንደሚሰራም ተገልጿል፡፡
 
በተጨማሪም ለ1ሺህአቅመ ደካማ አረጋውያን የቤት እድሳት የሚከናወን ሲሆን የችግኝ ተከላና የአካባቢ ፅዳት መርሀ ግብሮችም የሚከናወኑ ይሆናል።
 
በአጠቃላይ በመርሃ ግብሩ 200 ሚሊየን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣል መባሉን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬቴሪያት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.