Fana: At a Speed of Life!

የኪንታሮት ህመም ደረጃዎች፣ ምልክቶችና መከላከያ መንገዶች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኪንታሮት ህመም በፊንጢጣ ላይ የሚገኙ ደም መላሽ የደም ስሮች ሲያብጡ የሚፈጠር ነው፡፡

ህመሙ በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚከሰት ቢሆንም ከ45 እስከ 65 ዓመት ባሉት ሰዎች ላይ በብዛት ይከሰታል፡፡

በዋናነት በሁለት የሚከፈለው የኪንታሮት ህመም፤ አንደኛው ውጫዊ ኪንታሮት ሲሆን÷ በውጪኛው የፊንጢጣ ክፍል ላይ የሚከሰትና አብዛኛውን ጊዜ ሕመም የሚያስከትል ነው፡፡

ሁለተኛው ውስጣዊ ኪንታሮት ሲሆን÷ በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኝና አብዛኛውን ጊዜ ሕመም የማይኖረውና አራት ዓይነት ደረጃዎች ያሉት ነው።

አንደኛ ደረጃ፡- ይህ ደረጃ በፊንጢጣ ግድግዳ ላይ እብጠት ሲኖር ነው፤ እብጠቱ በዋናነት በስተ ግራ፣ በፊት ለፊትና በስተኋለኛው የፊንጢጣ ግድግዳ ላይ ይከሰታል፣

ሁለተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ የእብጠቱ መጠን ጨምሮ ለሽንት ሲቀመጡ በሚኖር ማማጥ እባጩ ወደውጪ ሲወጣና በራሱ ጊዜ ወደውስጥ ሲመለስ ነው፡፡

ሶስተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ እባጩ ለሽንት ሲቀመጡ ወደውጪ ይወጣና በራሱ ስለማይመለስ የግድ በእጅ መመለስ ሲፈልግ ነው፡፡

አራተኛ ደረጃ፡- በዚህ ጊዜ እባጩ ላይመለስ በፊንጢጣ ይወጣና ይቀራል፡፡

የሆድ ድርቀት፣ እርግዝና፣ የትልቁ አንጀት ካንሰር፣ ሽንት ቤት ተቀምጦ ለረጅም ጊዜ ማማጥ፣ ረጅም ጊዜ የቆየ ተቅማጥና የዕድሜ መጨመር አጋላጭ ሁኔታዎች የኪንታሮት ህመም አጋላጭ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

የኪንታሮት ህመም ምልክቶች ደግሞ ህመም የሌለው ከፊንጢጣ የሚፈስ ደማቅ ቀይ ደም፣ በፊንጢጣ አካባቢ ማሳከክ፣ ከፊንጢጣ የወጣ ሥጋ መሳይ እባጭና በፊንጢጣ አካባቢ የህመም ስሜት መኖር ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና ተቋም መሔድና ሐኪም ማማከር እንደሚያስፈልግ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኪንታሮት ህመም መከላከያ መንገዶች ምንድናቸው?

በፋይበር የበለፀጉ ምግቦችን መመገብ፣ ፈሳሽ በበቂ ሁኔታ መውሰድና የሆድ ድርቀትን ማስወገድ፣ ሰገራ በሚመጣ ጊዜ ጊዜውን ሳያሳልፉ ወደ ሽንት ቤት መሄድና መፀዳጃ ቤት ለረጅም ሰዓት አለመቀመጥ ከኪንታሮት ህመም መከላከያ መንገዶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.