Fana: At a Speed of Life!

በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት መንስኤን በመለየት መስራት አለብን – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 11፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የችግሮቹን መንስኤ በመለየት መስራት አለብን ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

በግሪክ አቴንስ እየተካሄደ ባለው የሴቶች የፖለቲካ መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት ንግግር፥ የሴት መሪዎች የፆታ እኩልነትን ጉዳይ የዕለት ተዕለት ንግግራቸው አካል አድርገው እንዲይዙ ጥሪ አቅርበዋል።

የጾታ እኩልነት ተግባራዊነቱ የተሟላ መሆን እንዳለበት አንስተው፥ ቢያንስ ስለጾታ እኩልነት በመናገር ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አፍሪካን በተመለከተም፥ መሪዎች በ2063 አጀንዳ ላይ ተመስርተው ለአህጉሪቱ መሻሻል መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በሴቶች ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ያላቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት የበለጠ ጥረት እንዲደረግም ጠይቀዋል።

በሴቶች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ከስር መሰረቱ ለማየት እና ችግሩን ለመፍታት ዋና ጉዳዩን ማየትና በዚህም ላይ በትኩረት መስራት አለብን ብለዋል ፕሬዚዳንቷ፡፡

በአፍሪካ ያሉ ሴቶችን ማብቃት እንደሚገባ ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ ያሉትን ሴቶች ቁጥር ለማሳደግ ብዙ ሴቶችን ወደአመራርነት ማምጣት ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በሁሉም የዓለም ክፍሎች ያሉ ሴቶች እያጋጠሟቸው ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።

በሴቶች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች እና ትንኮሳዎች ከቀን ወደ ቀን እየጨመሩ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች እስከመጨረሻው እልባት ለማበጀት ጥረቶችን ማድረግ አለብን ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ባለፈው ወር በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ “በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ማስቆም” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ረቂቅ ኮንቬንሽን ማፅደቁ በአህጉሪቱ ያሉ ሴቶችን ችግሮች ለመፍታት ተስፋ ሰጪ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.