Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 76 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት መፈጸሙ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል 76 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር የሚያወጣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት መፈጸሙን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡

ተቋሙ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት፣ በጸጥታ ሥጋቶች፣ በካሳ ክፍያ፣ በወሰን ማስከበርና ተያያዥ ጉዳዮች ከኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር)÷ በኃይል አቅርቦት ዘርፍ ተቋሙ እያከናወነ ያለውን የመሰረተ-ልማት ግንባታ ለባለድርሻ አካላት በማስገንዘብ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የምክክሩ ዓላማ ነው ብለዋል፡፡

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በሚገነባባቸውና በሚያልፍባቸው አካባቢዎች የደህንነት ጥበቃ ከማድረግ ጀምሮ የካሳ ጥያቄዎች እና የወሰን ማስከበር ጉዳዮችን ለመፍታት ክልሎችና በየደረጃው የሚገኙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ በ10 ቢሊየን ብር ሁለት የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እና ከ16 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በሚደርስ ወጪ ሰባት የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በነባርና አዲስ በሚገነቡ የኤሌክትሪክ መሰረተልማቶች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ወንጀሎች ተቋሙን ለኪሳራ እየዳረጉትና ፕሮጀክቶችንም እያጓተተ መሆኑን የኤሌክትሪክ ሃይል መረጃ ያመላክታል፡፡

በሁለት ዓመት ተኩል ውስጥ በስርቆት ብቻ 76 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም የወሰን ማስከበር ችግሮች እና ያልተገባ የካሳ ክፍያ መጠየቅ እንዲሁም በሠራተኞች ላይ የሚደርሱ የፀጥታ ስጋቶች በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት እየፈጠሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ከክልሉ የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው÷ ልማትን የሚያውኩ አሠራሮችን እንደማይታገሱና ለኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ጥበቃ ከተቋሙ ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።

የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ  የሚፈጸሙ ስርቆቶችን ለማስቀረት እና የሚታዩ የሕግና አፈጻጸም ክፍተቶችን ለማረም ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ብለዋል፡፡

ተቋሙ በክልሉ የሚያከናውናቸው ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነት ጥያቄዎች የሚመልሱ መሆናቸውን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.