Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በመንግስት ላይ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ጉዳት ያደረሰ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት በታክስ ሥርዓቱ ላይ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ ባደረገው ክትትል ነው ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር የዋለው፡፡

ተጠርጣሪው ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ እና ቴዎድሮስ ንጉሴ ወልድሀዋሪያ በተባሉ ሀሰተኛ ስሞችን በመጠቀም ከ2 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ በመንግስት ላይ ጉዳት ማድረሱ ተመላክቷል፡፡

ተጠርጣሪው በቁጥጥር ሥር ሊውል የቻለው ሐሰተኛ ስሞቹን በመጠቀም ከሌሎች ግብረ-አባሮቹ ጋር በመሆን ቴዎድሮስ ንጉሴ ሀያርያ በሚለው ስም ንግድ ፍቃድ በማውጣት ሲሆን÷ የወንጀል ድርጊቱ እንዳይደረስበትም ለማድረግ የተለያዩ የማጭበርበሪያ መንገዶችን ሲጠቀም ቆይቷል ተብሏል፡፡

ተጠርጣሪው ከታክስ ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ክትትል ለመሰወር በቦሌ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽ/ ቤት በመቀየር ህጋዊ በመምሰል የዕቃ እና አገልግሎት ግብይት ሳይኖር የተለያዩ ድርጅቶችና ግለሰቦች የመለያ ቁጥር LB 0019300 ከሆነው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ በ1 ሺህ 270 ደረሰኞች አማካይነት ምንም ሽያጭ ሳያካሄድ ደረሰኞችን ብቻ በመሸጥ መጠኑ 2 ቢሊየን 951 ሚሊየን 53 ሺህ 749.86 ብር የሚሆን ሽያጭ ማከናወኑ ታውቋል፡፡

በኢኮኖሚ ላይ ከሚፈጸሙ ግንባር ቀደም ወንጀሎች መካከል የታክስ ወንጀል አንዱ ሲሆን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለጉዳዩ ቅድሚያ ሰጥቶ ክትትል እያደረገበት እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ከሪፖርት አቅራቢ፣ ከባለድርሻ እና ከተለያዩ አካላት ከደረሱት መረጃዎች እና ከዳታቤዙ በመነሳት በወንጀል ድርጊቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ አገልግሎቱ የክትትል፣ የፍተሻና የመረጃ አቅርቦቱን አጠናክሮ የሚቀጥልና ከሌሎች የህግ አስከባሪ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራ መሆኑንም እንዳረጋገጠ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት መረጃ አመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.