Fana: At a Speed of Life!

ያልተመጠነ የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ታዳጊዎችን ለአዕምሮ ህመም እየዳረገ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ያልተመጠነ የሞባይል ስልክ አጠቃቀም ታዳጊዎችን ለአዕምሮ ህመም እያጋለጠ መሆኑን ጥናቶች አመላከቱ፡፡

አሜሪካዊው የማህበራዊ ስነ-ልቦና ባለሙያ ጆናታን ሃይት ይፋ ባደረጉት ጥናት እንዳመላከቱት÷ የአዕምሮ ህመም የሚያጋጥማቸው በአስራዎቹ እድሜ የሚገኙ ታዳጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

አሜሪካ ባሉ የኮሌጅ ተማሪዎች ላይ ባለሙያው ባካሄዱት ጥናት ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2018 ድረስ የስነ አዕምሮ ህመም ያለባቸው ታዳጊዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በ2020 ደግሞ ይህ ቁጥር በእጅጉ መጨመሩን ጠቅሰው፤ በተጠቀሰው ዓመት በአዕምሮ ህመም ድንገተኛ ክፍል በርካቶች ሊገቡ መገደዳቸውን አንስተዋል።

በአዕምሮ ህመም ምክንያት ራሳቸውን ለማጥፋት የሚሞክሩ ታዳጊዎች ቁጥርም የጨመረ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አሜሪካዊው የማህበራዊ ስነ-ልቦና ባለሙያ ምርምር፤ እነዚህ የአዕምሮ ጤና ችግሮች የሚመጡት በአብዛኛው ዘመናዊ ስልኮች ታዳጊዎች እጅ ላይ በቀላሉ መድረሳቸውን ተከትሎ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በስልኮቹ ምክንያት ህፃናት ከቤተሰብ እና ከጓደኞቻቸው ጋር ትንሽ ጊዜያትን ብቻ ያሳልፋሉ ያለው ጥናቱ÷ በአንፃሩ ታዳጊዎች በስልኮች ቀጥታ ጨዋታዎችን (ኦንላይን ጌም) በመጫወት እና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ ብሏል፡፡

በዚህም ታዳጊዎቹ ለኦንላይን ጌሞችና ለማህበራዊ ሚዲያ ሱሱ የሚጋለጡ ሲሆን ከዚህም ባለፈ ከእድሜያቸው ጋር የማይሄዱ እና ጎጂ የሆኑ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ሊመለከቱ እንደሚችሉ አስነብቧል፡፡

ታዳጊዎች ስቀው ተጫውተው እንጂ ትኩረታቸውን ስልክ ላይ አድርገው ማደግ የለባቸውም የሚለው ጥናቱ÷ ወላጆች የልጆቻቸውን ስልክ አጠቃቀም መወሰን እንደሚገባቸው እና በስልክ ምክንያት ከሚመጡ አደጋዎች ልጆቻቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባ አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.