በአዲስ አበባ “ምግባችንን ከጓሯችን” የተሰኘው የ2012 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ “ምግባችንን ከጓሯችን” የተሰኘው የ2012 የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርኃ ግብር በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረ።
መርኃግብሩን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና የግብርና ሚኒስትር ዑመር ሁሴን አስጀምረዋል።
በበጎ ፍቃደኛ የአዲስ አበባ ወጣቶች የችግኝ ተከላ እና የአካባቢው አርሶ አደሮችን ማሳ የማረስ የክረምት በጎ ፍቃድ ማስጀመሪያ መርኃ ግብር አቃቂ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 መንደር 6 ገላኒይዶሮ በተባለው አካባቢ ተካሂዷል።
ከዚህ በኋላ ለቀጣይ አራት ወራት የከተማዋ አርሶ አደሮችን ማሳ በበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች የማሳረስ እና በክረምት ችግኝ የመትከል ዕቅድን ለማሳካት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያዘጋጀው ይህ መርኃ ግብር በተለያየ የበጎ ፍቃድ ዘርፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል።