Fana: At a Speed of Life!

በጋዛ የተኩስ አቁም ዙሪያ ላይ የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በፀጥታው ምክር ቤት ውድቅ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የተዘጋጀውና በአሜሪካ አማካኝነት የቀረበው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውድቅ መደረጉ ተገለጸ፡፡

የፀጥታው ምክር ቤት በኒውዮርክ በሚገኘው የመንግስታቱ ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት በቀረበው የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ድምጽ ሰጥቷል።

የውሳኔ ሃሳቡን 11 ሀገራት ደግፈው አንድ ሀገር (ጉያና) ድምፀ ተዓቅቦ ስታደርግ፣ ሶስት ሀገራት ደግሞ ሩሲያ፣ ቻይና እና አልጄሪያ መቃወማቸው ተገልጿል።

ቻይና እና ሩሲያ የምክር ቤቱ ቋሚ አባላት በመሆናቸው ድምፅን በድምፅ በመሻር መብታቸውን በመጠቀማቸው ሰነዱ ውድቅ እንዲሆን ተደርጓል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ ከድምጽ መስጠት ሂደቱ በፊት ንግግር አድርገዋል፡፡

በንግግራቸውም አሜሪካ ከግብፅ እና ከኳታር ጋር በመሆን አስከፊውን የሰብአዊ ቀውስ ለመቅረፍ ይረዳናል በሚለው ስምምነት ዙሪያ ሌት ተቀን እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርድሩ ለስምምነት ቀርቦ እንደነበረና ነገር ግን እስከ አሁን እንዳልተፈፀመ ያነሱት አምባሳደሯ፤ የውሳኔ ሃሳቡ ወደዚህ ስምምነት ለመቅረብ እንደሚያግዝ አክለዋል።

ይሁን እንጂ የሩሲያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መልዕክተኛ ቫሲሊ ኔቤንዝያ ሀገራቱ የውሳኔ ሃሳቡን እንዳይደግፉ ጥሪ ማቅረባቸውን ስካይ ኒውስ ዘግቧል።

ቫሲሊ ኔቤንዝያ አክለውም ይህን ካደረጋችሁ እራሳችሁን በውርደት ትሸፍናላችሁ ሲሉም ነው የተናገሩት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.