Fana: At a Speed of Life!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ በኖርዌይ ከኖቤል ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኙ

አዲስ አበባ፣ህዳር 30፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በኖርዌይ ኦስሎ ከኖቤል ኮሚቴ አባላት ጋር ተገናኙ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2019 የዓለም የኖቤል የሰላም ተሸላሚ መሆናቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በኦስሎ በሚከናወን ስነ ስርዓትም ሽልማታቸውን ይቀበላሉ።

ባለፈው መስከረም 30 በኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሆነው መመረጣቸው የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በኖርዌይ ቆይታቸው ከሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤርና ሶልቤርግ እና ከንጉስ ሃራልድ 5ኛ ጋር ውይይት የሚያደርጉ ሲሆን፥ የሀገሪቱን ፓርላማም ይጎበኛሉ ተብሏል።

ዛሬም በኦስሎ ከተማ የስብሰባ አዳራሽ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ከወጣው መርሃ ግብር ማወቅ ተችሏል።

ዶክተር አብይ ለሰላም እና ለዓለም አቀፍ ትብብር ላደረጉት ጥረት በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ለዓመታት የዘለቀው የድንበር የይገባኛል ውዝግብ በሰላም እንዲፈታ ተነሳሽነትን በመውሰዳቸው የ2019 የኖቤል የሰላም ተሸላሚ እንዳደረጋቸው ኮሚቴው መግለፁ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ሁሉም ባለደርሻ አካለት በኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በሰሜን ምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም እና እርቅ እንዲመጣ ላደረጉት አስተዋፀኦ እውቅና ለመስጠትም እንደተመረጡ ኮሚቴው ገልጿል።

ኮሚቴው በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ከኤርትራ ጋር ሰላም ለማምጣት ቃል መግባታቸውን በማስታወስ፥ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመቀበል ሀገራቱ አስመራ ላይ የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ማስቻላቸውን ነው ያነሳው።

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሰላም ስምምነት በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሻክሮ የነበረው የጅቡቲና ኤርትራ ግንኙነት እንዲስተካል ሚና እንደነበራቸው አስታውሷል።

የኖቤል ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ለረጅም አመታት የነበረው ውጥረት እንዲፈታ ተነሳሽነት ሲወስዱ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ሀሳቡን በበጎ መልኩ ተቀብለዋል ብሏል።

ከዚህ ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሃላፊነት ከመጡ በኋላ በርካታ ለውጦችን በመካሄድ የሀገሪቱ ዜጎች ለተሻለ ህይወት ተስፋ እንዲያደርጉ አድርገዋል ብሏል ኮሚቴው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.