Fana: At a Speed of Life!

ከመጋቢት አጋማሽ ጀምሮ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከመጋቢት አጋማሽ እስከ ግንቦት መጨረሻ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አሳሰበ፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለማ መሠለ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ በክልሉ ደጋማ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው የበልግ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም ጎርፍና ናዳ ሊኖር ስለሚችል በአካባቢው የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በተለይም የመሬት መንሸራተት በተደጋጋሚ በሚከሰትባቸው እንዲሁም ገደላማና ተዳፋት አካባቢዎች ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥንቃቄ ማድረግ ይገባቸዋል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

ዝናቡ በደረሱ ሰብሎች ላይም ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል አርሶ አደሮች የደረሱ ሰብሎችን በጊዜ መሰብሰብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ሕጻናትንና እንስሳትን ከመዝነቡ በፊት ወደ ቤት ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመው÷ ዝናብ ከጀመረ በኋላም እስኪያቆም ድረስ እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠብ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ሕብረተሰቡ የጎርፍ መፋሰሻ ቦታዎችን ማዘጋጀትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.