Fana: At a Speed of Life!

የስኳር ህመምን ለመከላከል ምን ጥንቃቄዎች ሊወሰዱ ይገባል?

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የስኳር ህመም በደም ውስጥ የስኳር መጠን ከሚገባው በላይ ሆኖ በሚገኝበት ሰዓት የሚከሰት ተላላፊ ያልሆነ የህመም አይነት ነው።

በዚህም በዋናነት የህመም መከላከያ መንገድ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትና የአኗኗር ዘይቤ መከተል ሲሆን÷ በዚህ ውስጥ ደግሞ ብዙ አይነት ድርጊቶች ይካተታሉ፤ አንደኛው የሰውነት ክብደትን መቆጣጠር ነው።

የሰውነት ክብደታችን ከአቋማችን ጋር የተመጣጠነ መሆን አለበት፣ ይህ እንዲሆን ደግሞ አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው።

ሌላው ጣፋጭና ቅባት የበዛባቸው ምግቦችንና የፋብሪካ ምርቶችን ከመመገብ መቆጠብ ነው፡፡

በእነዚህ ፈንታ አትክልትና ፍራፍሬ አዘውትሮ መመገብ፤ የሰውነት ክብደታችንንና አቋማችንን የሚያመጣጥኑ ምግቦችን አመጣጥኖ መውሰድ የተሻለ የስኳር ህመምን የመከላከል አቅም ያሳድጋል።

በስኳር የመያዝ እድልንም በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀንስ ነው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ የሚያመላክተው፡፡

ከዚህ ባሻገር አዘውትሮ ምርመራ ማድረግ አንዱ የስኳር ህመምን ለመከላከል በእጅጉ የሚያግዝ ነው፤ ምክንያቱም በተለይ ቅድመ ስኳር ደረጃ ላይ እያለ የስኳር ህመምን ማግኘት ከተቻለ የተለያዩ የህክምና አይነቶችን በመውሰድ ወደ መደበኛና ጤናማ የስኳር መጠን መመለሱ በጣም ቀላል ነው።

ስለዚህ አንድ ሰው እድሜው ከ30 እና 40 ዓመት ካለፈ አዘውትሮ ምርመራ ማድረግ ያለበት ሲሆን÷ ይህ ካልሆነ ግን ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ የስኳር ምርመራ ማድረግ የግድ ይላል።

እነዚህን የቅድመ መከላከያ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ የስኳር በሽታ ተጋላጭነትን መቀነስ ይቻላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.