Fana: At a Speed of Life!

ዌንዡ ኒክሲን ትሬዲንግ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ወረቀት የማምረት ፍላጎት አለኝ አለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) 300 ሚሊየን ዶላር ካፒታል ያለው የቻይናው ዌንዡ ኒክሲን ትሬዲንግ ኩባንያ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ወረቀት የማምረት ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ ከኩባንያው አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የኩባንያው አመራሮች ስለ ኢንቨስትመንት ዕቅዳቸው ዝርዝር መረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

አቶ አክሊሉም በኮርፖሬሽኑ የሚገኙ የኢንቨስትመንት ማዕከሎችን፣ ማበረታቻዎችን፣ የመሰረተ-ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥን የተመለከቱ መረጃዎችን አስረድተው÷ ኮርፖሬሽኑ ለኩባንያው ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደረግ አረጋግጠዋል።

ከውይይቱ ባሻገር የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ የሚገኘውን ቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝታቸውም በፓርኩ ለባለሀብቶች የሚቀርቡ እንደ መብራት፣ ውኃ እና ቴሌኮም የመሳሰሉ አገልግሎቶች ክፍያ ከሌሎች ተመሳሳይ ሀገራት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን ተገንዝበናል ብለዋል፡፡

ይህም በፓርኩ ኢንቨስትመንት ለማድረግ እንድንወስን ከፍተኛ ሚና አበርክቷል ማለታቸውን የኮርፖሬሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡

ዌንዡ ኒክሲን ትሬዲንግ በፈረንጆቹ 2011 የተቋቋመና ተቀማጭነቱን በቻይና ያደረገ ኩባንያ ሲሆን÷ በሳዑዲ ዓረቢያ፣ ጋና፣ ናይጄሪያ፣ ኢራን እና አዘርባጃን በፋይበር፣ ሴራሚክ፣ አልሙኒየም እንዲሁም ሌሎች የምርት አይነቶች የተሰማራ ተቋም መሆኑም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.