Fana: At a Speed of Life!

በተፈጥሮ የሚከሰት የልብ ህመም ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በተፈጥሮ የሚከሰት የልብ ህመም መንስኤው የማይታወቅና ልንከላከለው የማንችለው ተፈጥሯዊ የጤና ችግር መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የህጻናት ስፔሻሊስትና የህጻናት የልብ ሃኪም ዶ/ር ታደሰ ጌታሁን ÷በተፈጥሮ የሚከሰት የልብ ህመም በአፈጣጠር ጊዜ የሚፈጠር የልብ ክፍተት ወይም ጥበት ፣ የአንዱ የልብ ክፍል ከሌላኛው የልብ ክፍል መገናኘት እንዲሁም የልብ ቱቦ መገናኘት ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

የተፈጥሮ የልብ ችግር ያለበትን ህጻን መለየት የሚቻልበት ዘዴ ሲያስረዱም ህጻናት ሲወለዱ ከንፈራቸው የመጥቆር ምልክት ካሳዩና በ”ስቴቶስኮፕ” ሲደመጥም ደም ወደ ልብ ሲረጭ የሚሰማ ለየት ያለ ድምጽ ካለ የልብ ምርመራ በማድረግ መለየት ይቻላል ብለዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜም ህሙማን ሌላ የጤና እክል ገጥሟቸው ሲመጡ በሚያደርጉት ምርመራ ሊታወቅ እንደሚችል ዶ/ር ታደሰ ይናገራሉ፡፡

ችግሩ ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ ሊቆይ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለም አስረድተዋል፡፡

በተፈጥሮ የሚከሰት የልብ ክፍተት የሚከሰትበት መጠን እንደ አጠቃላይ ሲታይ አንድ በመቶ ሲሆን÷ ይህ ችግር በህመሙ ተጠቂ ህጻን እድገት ላይም ይሁን የጤና ሁኔታ ላይ የሚያስከትለው ችግር የከፋ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይህ የተፈጥሮ የልብ ህመም ችግር በአብዛኛው መነሻው ምን እንደሆነ የማይታወቅ ሲሆን÷ በጄነቲክና ከዘረመል ችግር እንዲሁም በእርግዝና ጊዜ አልኮል በመውሰድና በኬሚካል በመጋለጥ ችግሩ ሊፈጠር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡

በተፈጥሮ የሚከሰት የልብ ክፍተት ችግር በእርግዝና ጊዜ በሚደረግ ምርመራ ሊታወቅ እንደሚችል ገልፀው ህጻኑ ከተወለደ በኋላ በሚደረግ ቀዶ ጥገና መስተካከል የሚችል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
ለዚህ የተፈጥሮ የልብ ህመም ችግር በመድሃኒት የሚሰጠው ህክምና ለጊዜያዊ ፈውስ እንጂ ችግርሩን በዘላቂነት የሚፈታ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.