Fana: At a Speed of Life!

በአሜሪካ ከባልቲሞር ድልድይ መደርመስ ጋር ተያይዞ ወንዝ ውስጥ የጠፉ ሰዎችን ፍለጋ ቀጥሏል

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ የባልቲሞር ድልድይ መደርመስ ጋር ተያይዞ የነፍስ አድን ሰራተኞች ወንዝ ውስጥ የጠፉ ሰዎችን በመፈለግ ላይ መሆናቸው ተገለጸ፡፡

በአሜሪካ ባልቲሞር ከተማ ውስጥ የሚገኘው ትልቅ ድልድይ ኮንቴይነር በጫነ መርከብ ተገጭቶ በመደርመሱ በፓታፕስኮ ወንዝ ውስጥ ወድቋል።

በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጠዋት ላይ አደጋ የደረሰበት ድልድይ በሰዓቱ ጉዞ ላይ ከነበሩ ተሽከርካሪዎች እና ሰዎች ጋር ነው ውሃ ውስጥ መግባቱ ነው የተገለጸው።

እስከ አሁን ሁለት ሰዎች ከውኃው ውስጥ ማውጣት መቻሉን የተናገሩት የአካባቢው ባለስልጣናት ቢያንስ ሰባት ሰዎችን የማፈላለግ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

መርከቧ አሁን ሶስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ካለው እና የዋናው መንገድ አካል ከሆነው ከፍራንሲስ ስኮት ኪ ድልድይ ፍርስራሽ ሥር እንደምትገኝም ተጠቁሟል።

ድልድዩ በሚፈርስበት ጊዜ አንዳንድ የግንባታ ሰራተኞች በድልድዩ ላይ እንደነበሩ የገለፁት የከተማው ከንቲባ፤ ክስተቱ ተነግሮ የማያልቅ አሳዛኝ ነው ብለውታል።

በውሃ ውስጥ መፈለጊያ መሳሪያ (ሶናር) በመታገዝም ከውሃ ውስጥ ብዙ ተሽከርካሪዎችን ማግኘት መቻሉን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

አደጋው ሆን ተብሎ የተፈፀመ ስለመሆኑ የሚጠቁም ነገር ባይኖርም የአደጋውን መንስኤ ለማወቅ በጣም ገና ነው ሲሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል፡፡

በድልድዩ አቅራቢያ ያለው የባልቲሞር ወደብ በአሜሪካ ውስጥ ለልዩ የጭነት መርከቦች ግዙፉ መሆኑ ተነግሯል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.