Fana: At a Speed of Life!

ኬንያ ከ18 ሺህ በላይ የምሽት ቤቶች እንዲዘጉ አደረገች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኬንያ መንግስት ከ18 ሺህ በላይ በሚሆኑ የምሽት ቤቶች እና የመጠጥ አምራቾች ላይ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል፡፡

እርምጃው የሀገሪቱ መንግስት የአልኮሆል እና አደንዛዥ ዕፅ ሱሰኝነት ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት አካል መሆኑ ነው የተገለለፀው፡፡

የኬንያ ምክትል ፕሬዚዳንት ሪጋቲ ጋቻጓ÷ መንግስት ህገ-ወጥ የአልኮል እና የአደንዛዥ እፅ ዝውውርን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በዚህ ውሳኔ ከአንዳንዶች ተቃውሞ እንዳጋጠመ ጠቅሰው÷ መንግስት ህገ-ወጥ የአልኮል ዝውውርን ለመከላከል የወሰደውን አቋም እንደማይቀይር አረጋግጠዋል፡፡

በሀገሪቱ የፀረ-አልኮሆል ንቅናቄ ከ20 ቀናት በፊት የተጀመረ ሲሆን እስካሁን ከ18 ሺህ በላይ የምሽት ቤቶች ሲዘጉ ከህገ ወጥ የአልኮሆል ዝውውር ጋር በተያያዘ 258 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

በተጨማሪም በትምህርት ቤትና በሌሎች ተቋማት አቅራቢያ የሚገኙ ከ5 ሺህ በላይ የአልኮሆል ማከፋፈያዎች የንግድ ፍቃዳቸው እንዲሰረዝ እና እንዲዘጉ መደረጋቸው ተመላክቷል፡፡

እንዲሁም ከአደንዛዥ እፅ ዝውውር ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የሚገኙ 22 ፋርማሲዎች እንዲዘጉ መደረጋቸውም የተገለፀ ሲሆን ከመደበኛው ሰዓት ቀድመው በሚከፈቱ የምሽት ቤቶች መንግስት እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን አርቲ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.