Fana: At a Speed of Life!

የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ ህመም ምንነትና መንስዔዎች

 

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አብዛኛውን ጊዜ ከወጣትነት የእድሜ ክልል አንስቶ እስከ እርጅና ያሉ የሰዉ ልጆችን በሙሉ ሊያጠቃ የሚችል ህመም የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ ህመም በተለምዶ (sciatica) ተብሎ ይጠራል።

የሚሰራጭ የወገብ የነርቭ ዘንግ ህመም ሲባል ህመሙ ከአንደኛው ወገብ ጀምሮ ወደ ታች ደረጃ በደረጃ የሚሰማ ህመም ነው።

ምልክቶቹም ከወገብ ጀምሮ ዳሌ – ጭን – እግር ድረስ በተለያየ መጠንና አቅጣጫ የሚሰማ የማቃጠል፣ መለብለብ፣ መጋል መንደድ፣ መደንዘዝና የመስነፍ ስሜቶች ናቸው።

ምልክቶቹ አንዳንድ ሰዎች ላይ ሲቀመጡ፣ ሲጓዙ፣ በጀርባ ሲተኙ፣ በጎን ሲተኙ ህመማቸው ሊባባስ ይችላል፤ በሌሎች ደግሞ በነዚህ አጋጣሚዎች ሊሻላቸው ይችል ይሆናል።

ከህመሙ በተጨማሪ እንደ በረዶ መቀዝቀዝ፣ አልፎ አልፎም የጡንቻ መዛል ተያያዥ የችግሩ ምልክቶች ሆነው እንደሚታዩ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ አጋላጭ መንስዔዎቹ:-

እግርን ለብዙ ጊዜ አጣምሮ መቆየት – እግር ሲጣመር በታችኛው ወገብና በዳሌ ላይ ባሉ የጡንቻና አጥንት አቀማመጥ ላይ ለውጥ እንዲመጣ ያደርጋል፤ ይኸ ሲሆን ተሹለክልከውና ተጠማዘው በሚጓዙ የነርቭ ዘንጎች ላይ አካላዊ ጫና ያሳድራል።

በኋላ ኪስ ቦርሳ (ዋሌት) አድርጎ መቀመጥ – የኪስ ቦርሳ በተለይ በወረቀቶች የተወጠረ ኪስ አድርጎ መቀመጥ በዳሌ ጡንቻ ላይ ችግር ይፈጥራል፤ ጡንቻዎቹ ሲጎዱ ሸፍነው በሚያሳልፏቸው የነርቭ ዘንጎች ላይ ጉዳት ይፈጥራል።

የተዛባ አቀማመጥ – ይህ የሰውነት ክብደት ምጥጥንን ያልጠበቀና ተፈጥሯዊ የነርቭ መሿለኪያ መስመሮችን የሚያጠብ በመሆኑ ለከፋ የነርቭ ችግር አጋላጭ ነው።

ሲቀመጡ ወደ አንድ አቅጣጫ ሳያዳሉ ለግራና ቀኝ ክፍሎች እኩል በሆነ መጠን መቀመጥ ተገቢ ነው። ሌላው ደረቅ ነገር ላይ አብዝቶ መቀመጥ እና በጀርባ ሸክም መሸከም ለጉዳት ያጋልጣል።

በተጨማሪም የአጥንት መሳሳት፣ የፀሐይ እጥረት፣ የአጥንት ማደግ፣ የነርቭ መውጫ መሿለኪያዎች መጥበብ፣ የመገጣጠሚያ ብግነትና መጋጨት እንዲሁም የዲስክ መንሸራተት ዋና መንስኤዎች ናቸው።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የነርቭ መሿለኪያ መጥበብ በጣም በዝቶ ይገኛል፤ እንደዚህ አይነት ህመም በነፍሰ ጡር እናት ላይ ሊከሰት ይችላል።

ዘልማዶችን ማስቀረት፣ ሸክምን ማስቀረት፣ ፀሐይ መሞቅ፣ ክብደትን ማስተካከል፤ አመጋገብን ጤናማ ማድረግ፣ ሲጋራ አለማጨስ፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ደግሞ የሚሰራጭ የወገብ ነርቭ ህመምን መከላከያና ማከሚያ ስልቶቹ ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.