Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2012 በጀት ዓመት 10 ወራት ከወጪ ንግድ 2 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ፥ በ10 ወራቱ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ መሰራቱን አስታውቀዋል።

አፈፃፀሙ በ2011 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወራት ከተገኘው 2 ነጥብ 15 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ12 ነጥብ 6 በመቶ ብልጫ ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ጫት ከእቅድ በላይ ሲያስመዘግቡ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጨርቃጨርቅና አልባሳት፣ የጥራጥሬ ሰብሎች፣ ስጋ፣ ቅመማ ቅመም እና ወርቅ ደግሞ የእቅዳቸውን ከ50 እስከ 99 በመቶ ክንውን አስመዝግበዋል።

በሌላ በኩል ከተያዘው ዕቅድ አንጻር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ከ50 በመቶ በታች ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ የወጪ ንግድ ምርቶች ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እና የቁም እንስሳት ናቸው።

የምርት ትንተናና የክምችት ክትትል በማድረግ በተገባው የኮንትራት ውል መሰረት እንዲላክ ድጋፍ ማድረግ፣ በህገ ወጥ መንገድ በክምችት የተያዙ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲገቡ መደረጉ፣ አንዳንድ ከተሞች ከፍተኛ ህገ ወጥ የምርት ክምችት መኖሩን በድንገተኛ ቆጠራና ክትትል በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እተወሰደ መሆኑና በተለይም ከጉሙሩክ ኮሚሽንና ከክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት የኮንትሮባንድ ቁጥጥር እና ህገ ወጥ ንግድ ማጠናከር መቻሉ ለገቢው መጨመር ምክንያት ነው ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.