Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ እና ሕንድ ታሪካዊ ወዳጅነት ሲወሳ …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሕንድ ለሦስት ሣምንታት ያደረጉት ጉብኝት በዘመናዊው የዲፕሎማሲ ታሪክ የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ጅማሮ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በፈረንጆቹ 1956 ለመጀመሪያ ጊዜ ሕንድን መጎብኘታቸው ይታወሳል፡፡

ሕንድ ሲደርሱም የንጉሥ የክብር አቀባበል ተደርጎላቸዋል፤ በጀልባ ሙምባይ ከተማ በደረሱ ጊዜም የሀገሪቱ ጦር ጀልባዋን በማጀብ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል፡፡

በወቅቱ የሙምባይ ከፍተኛ ባለስልጣን ሞራርጂ÷ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቀባበል 21 ጊዜ መድፍ እንዲተኮስ በማድረግ ያላቸውን ክብር አሳይተዋል፡፡

ንጉሡም በቆይታቸው በብራቦርን ከተማ በሕንድ እና በአውስትራሊያ መካከል የተደረገውን የክሪኬት ስፖርት ከመታደም በተጨማሪ በሰሜን እና ምሥራቃዊ ሕንድ ሦስት ሣምንታትን የፈጀ ጉብኝት አድርገዋል፡፡

ጉብኝታቸውም በፈረንጆቹ 1955 የተካሄደውን የእስያ-አፍሪካ ጉባዔ ተከትሎ በአፍሪካ እና በእስያ ሀገራት መካከል ያለው ትብብር እያደገ በመጣበት ወቅት የተደረገ መሆኑ ይገለፃል፡፡

የሕንድ መንግሥትም በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያደረጉት ጉብኝ ታሪካዊ ትስስር ላላቸው ሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደነበረው መግለጹ ይታወቃል፡፡

የያኔው የንጉሡ የሥራ ጉብኝትም በኢትዮጵያ እና ሕንድ መካከል አሁን ላለው የጠነከረ ወዳጅነት መሠረት መጣሉ ይነገራል፡፡

በጉብኝታው ወቅትም በወቅቱ የሕንድ ፀረ-ቅኝ ግዛት አቀንቃኝ የነበሩት ጃዋሃርላል ኔህሩ÷ ፋሽት ጣልያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅትም የፋሺስቱን ወረራ በመቃወም ለኢትዮጵያ ላሳዩት ድጋፍ ንጉሡ ማመስገናቸው ይታወቃል፡፡

በፋሺስት ወረራ ወቅት ከኔህሩ በተጨማሪ የድሮው የጃንጂ (የአሁኗ ሬይጋድ) አውራጃ ገዥ የነበሩት ናዋብ ሳኅብ ሲዲ አርማድ ካን÷ ሠራዊታቸውን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጣልያንን መዋጋት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን ዘ ቴሌግራፍ በወቅቱ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.