Fana: At a Speed of Life!

ህብረተሰቡ በኮቪድ19 ስጋት በጤና ተቋማት የሚያገኘውን የህክምና አገልግሎት ማቋረጥ የለበትም – ዶክተር ሊያ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 1 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ስጋት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የሚያገኘውን የህክምና አገልግሎት ማቋረጥ እንደሌለበት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ዶክተር ሊያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የኮቪድ19 ወረርሺኝ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ቫይረሱን ለመከላከል የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

ለአብነትም ባለፈው አንድ ሣምንት ብቻ 848 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸውና 16 ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል።

በጽኑ ህሙማን ክፍል የሚገኙ ሰዎች ቁጥር በማሻቀብ አሁን ላይ 32 መድረሱን ገልጸው፥ የተለያዩ ድጋፎች እየተደረገላቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።

የበርካታ ሰዎች በቫይረሱ መያዝና ለሞት መጋለጥ ለተለያዩ አገልግሎቶች ወደ ህክምና ተቋማት ሰዎች እንዳይመጡ ምክንያት መሆን የለበትምም ነው ያሉት።

ግለሰቦች ወደ ጤና ተቋማት ባለመሄድ ለአላስፈላጊ የጤና ችግሮች እየተጋለጡ ነው ያሉት ሚኒስተሯ፥ ይህ አይነቱ አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በቤታቸው ህይወታቸው የሚያልፉ ሠዎችን ቫይረሱ እንዳለባቸውና እንደሌለባቸው ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ እንዳይካሄድ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ ትክክል አለመሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ ምርምራው የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ ስለሚኖረው ኅብረተሰቡ ተባባሪ እንዲሆን መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.