Fana: At a Speed of Life!

አፈ- ጉባዔዋ በጠሩት የምክር ቤቱ መደበኛ ሰብሰባ ዋዜማ የመልቀቂያ ውሳኔ መስጠታቸው ተገቢነት የለውም- ፌዴሬሽን ምክር ቤት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አፈ-ጉባኤዋ በጠሩት የምክር ቤቱ መደበኛ ሰብሰባ ዋዜማ የመልቀቂያ ውሳኔ መስጠታቸው ተገቢነት የሌለውና እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካይ ኃላፊነት ትክክለኛ ያልሆነ ውሳኔ እንደሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።

አፈጉባዔዋ ዛሬ ልዩነት አለኝ ብለው በሚዲያ ከመናገራቸው በቀር በእርሳቸው ከሚመራው አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር ምንም አይነት ልዩነት እንዳልነበራቸውም ገልጿል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ የፌዴሬሽኑን ምክትል አፈጉባዔ ጨምሮ የምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ምክትል አፈጉባዔው አቶ መሃመድ ረሽድ ሃጂ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከነገ በስትያ መደበኛ ስብሰባ ለማካሄድ በእርሳቸው ከሚመራው አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በጥሩ ሁኔታ ተወያይተውና አጀንዳዎችን አጽድቀው እንደነበር ገልጸዋል።

አንድ የምክር ቤት አባል የስራ መልቀቂያ ሲያስገባ የራሱ ደንብና ስነ-ሥርዓት ቢኖረውም የአፈ-ጉበዔዋ ውሳኔ ግን ከዚህ ደንብና መመሪያ ያፈነገጠ ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል።

በመደበኛ ስብሰባውም አባላቱ መጠራታቸውን ተከትሎ በተያዘለት ዕለት እንደሚካሄድም ገልጸዋል።

አፈጉባዔዋ እንደ ምክር ቤት አባል በመደበኛ የምክር ቤቱ ውይይቶች ላይ የፓርቲያቸውን አቋምና በምክር ቤቱ ያላቸውን ኃላፊነት በተለያየ አግባብ እንደሚያስተናግዱ መግለጻቸውንም አቶ መሃመድ አስታውሰዋል።

ምናልባትም በራሳቸው በኩል ተጽዕኖ ተደርጎባቸው ካልሆነ በቀር በምክር ቤቱ አባላት የደረሰባቸው ምንም አይነት ጫና እንዳልነበረ ጠቁመዋል።

በምክር ቤቱ የሕገመንግስትና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ጸሃፊ አቶ ወርቁ አዳሙ በበኩላቸው ምክር ቤቱ በዓመት ቢያንስ ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብስባ እንደሚያካሂድ ገልጸው፤ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ይኸው ሊደረግ መወሰኑን ተናግረዋል።

አስተባባሪ ኮሚቴው አምስት አጀንዳዎችን በጋራ ቀርጾ ማጽደቁን፤ ሰኔ 1 እና 2 ማለትም ዛሬ እና ነገ ደግሞ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለማድረግ ተወስኖ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም ከኮቪድ19 ጋር በተያያዘ፣ በግለሰብና በቡድን ጥያቄዎች ትርጉም፣ በደቡብ ኢትዮጵያ የክልልነት ጥያቄዎች፣ ከሕዝብና ቤት ቆጠራ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አጀንዳዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

እስካለፈው ሐሙስ ድረስ የምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ በመጪው ሰኔ 3 ቀን በራሳቸው ደብዳቤ መጥራታቸውንና በቀረቡ አጃንዳዎች ላይም ምንም ልዩነት እንዳልነበራቸውም ገልጸዋል።

አፈጉባዔዋ ጥያቄዎች ቢኖሯቸው እንኳን ለምክር ቤቱ አቅርበው በስነሥርዓቱ መሰረት መልቀቅ እንጂ በምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ዋዜማ አስተባባሪ ኮሚቴው ሳያውቅ በሚዲያ መናገራቸው ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም ብለዋል።

በአፈጉባዔዋ መልቀቅ በቀጣይ በምክር ቤቱ አጀንዳዎችና በመደበኛ ስራው ላይ ምንም የሚያስተጓጉለው ሂደት የለም፤ ሁሉም አጀንዳዎች በቂ ቅድመ ዝግጅት ስለተደረገባቸው ይካሄዳሉ ብለዋል።

ነገር ግን ራሳቸው በጠሩት መደበኛ ስብሰባ ዋዜማ መልቀቃቸው፣ የፓርቲ ወገንተኝነታቸው የብሔር ብሔረሰብ ተወካይነታቸውን ያሳነሰና ተገቢነት የሌለው ውሳኔ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የአፈጉባዔዋን ውሳኔ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጣቸውን ኃላፊነትና እምነት ማጉደል አድርገው እንደሚቆጥሩት ገልጸው ድንገት በሚዲያ ወጥተው መናገራቸውም ድብቅ ዓላማ እንዳለው ያሳያል ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.