Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ክልላዊ ኮንፈረንስ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የብልፅግና ፓርቲ ክልላዊ ኮንፈረንስ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቅቋል፡፡

ክልላዊ ኮንፈርንሱ ከመጋቢት 21 እስከ 23 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልፅግና” በሚል መሪ ሃሳብ ነው በባሕር ዳር ከተማ ሲካሄድ መቆየቱን የአሚኮ ዘገባ አመልክቷል።

የአቋም መግለጫ ነጥቦቹም እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

1ኛ. ፓርቲያችን ብልፅግና ተቋማዊ መሰረት ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት፣ በወንድማማችነት እሴት ላይ የቆመ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከርና እና ብዝኃ ልሳን የሆነ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ሰፊ ርብርብ ሲያደርግ ቆይቷል። ለውጡን ተከትሎ በሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎች በተለይም ገዳቢ የነበሩ የጸረ ሽብር አዋጅ፣ የሚዲያ ሕግ፣ የሲቪክ ማኅበራት እና የመሳሰሉት ሕጎች እንዲሻሻሉና ተግባራዊ እንዲሆኑ በመደረጉ ዜጎች ሕግን መሰረት አድርገው የመሰላቸውን እንዲደግፉ እና ያልተመቻቸውን እንዲቃወሙ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸዋል፡፡
የተጀመረው ሀገራዊ አካታች የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከምርጫ ማግስት ተቋማዊ መሰረት እንዲኖረው ወደ ተቋም ግንባታ ተገብቷል። የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ እና ሌሎች ተቋማት ከማንኛውም ተጽዕኖ ነፃ ሆነው መሥራት እንዲችሉ አቅማቸው እንዲጎለብትና የአስተዳደር ነፃነት እንዲያገኙ ሆነው እንዲደራጁ ተደርጓል።

በመሆኑም በሀገር ግንባታ ሥራችን ላይ ወጣ ገባ የሆነ አፈፃፀም ቢኖርም በብዙ ቦታዎች በተለይም በክልላችን ተስፋ ሰጭ ውጤቶች ታይተዋል፡፡ ስለሆነም እኛ የብልፅግና ፓርቲ አባላት በሀገራችን ብሎም በክልላችን የተጀመሩ የኅብረ – ብሔራዊ ፌደራላዊ ስርዓተ መንግሥት ግንባታ ሥራዎች በተለይም በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ የበኩላችንን ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን!

2ኛ. የዘመናዊት ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክን ተንተርሰው በተንሠራፉ አሉታዊ ትርክቶች ምክንያት የሀገርን ሠላምና የሕዝብን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡የበርካታ ዜጎች ሕይወት መጥፋት፤ የአካል ጉዳት፤ የሥነ ልቦና ስብራትና ንብረት ውድመት ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ይህንን አንገብጋቢ ችግር በውል ያጤነው ፓርቲያችን ብልጽግናም ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በሚያስችል መልኩና በሀገራችን ያለውን ብዝኃነት መሰረት ባደረገ አካታች ሕዝባዊ ምክክር ችግሩን ከስሩ ለመንቀል የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች፤ አሠራሮችና ይህንን የማስፈጸም አቅም ያላቸው ነጻና ገለልተኛ ተቋማት ተቋቁመው ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡በሂደቱም ተስፋ ሰጭ አበረታች ውጤት ተገኝተውበታል፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬም ቢሆን የተሻለ ሀገራዊ መግባባት፤ ጠንካራ መተማመንና ተደጋግፎ የመሥራት ባሕልን የማጎልበት እንዲሁም የተሸረሸሩ እሴቶቻችንን ለማደስ የሚረዱ ሥርዓቶችን መገንባት እንደሚገባ በዚህ ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ዘንድ የወል ድምደሜ ተደርሶበታል፡፡

በመሆኑም ፓርቲያችን ብልጽግና በሀገራችን የትኛውም ክፍል ላይ የተስተዋሉ አለመግባባቶችን፤ የሠላም እጦቶችን እንዲሁም አውዳሚ ግጭቶችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ የበላይነት የማስከበር ግዴታችንን ከመወጣት ጀምሮ እስከ የሠላም አማራጮችን መጠቀም ድረስ የደረሱ ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡

ሥለሆነም በየትኛውም የሀገራችን ክፍል፤ ማንኛውም ዓይነት የአስተሳሰብ ልዩነቶች በዜጎች ሁለንተናዊ ደህንነትና በሀገር አንድነት ላይ የስጋትና የአደጋ ምንጭ የሚሆኑበት ምዕራፍ እንዲያበቃ፤ ሁሉም አይነት ግጭቶች በሰላማዊ አማራጭ ብቻ እንዲፈቱ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነት እያረጋገጥን መላው ሕዝባችን ከፓርቲያችን ብልጽግና ጎን እንዲሰለፍ ልባዊ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

3ኛ. ፓርቲያችን ብልፅግና ከለውጡ ማግስት የኢኮኖሚ እድገታችንን ካለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተሻለ መንገድ ለማስቀጠል በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃግብር ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ ማነቆዎችን በመለየትና ማነቆዎችንም ለመፍታት የሚያስፈልጉ አቅጣጫዎችን በማመላከት ሰፊ ርብርብ አድርጓል፡፡ አካታችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያረጋግጥ የብዝሃ ዘርፍ የልማት አቅጣጫን በመከተልና የአረንጓዴ አሻራ ስራችንን በማጠናከር በአለምዓቀፍ ደረጃ አስደማሚ ውጤት እንደተመዘገበ እኛ የዚህ ኮንፈርንስ ተሳታፊዎች በዝርዝር ገምግመናል፡፡

ስለሆነም የሀገራችንን ኢኮኖሚ በሚያሳድጉ፣ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ በሚያደርጉ የሌማት ትሩፋት ስራዎች ላይ ማተኮር እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በሚያረጋግጡ የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ማተኮር እጅግ ወሳኛ ተግባር በመሆኑ እኛ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የድሃውን ማኅበረሰብ የኑሮ ሁኔታና ደረጃ ያገናዘበ የዋጋ ማረጋጋት ሥራ ላይ ስንሠራ የነበረውን የበለጠ ተኩረተ ለመስጠት፤ የግብርና ምርትን በሚያሳድጉ ተግባራት ላይና ለኢንዱስትሪ ግብአት በሚሆኑ የግብርና ምርቶች ማምረት ላይ ማተኮር ኢንዳለብን መግባባት ላይ የደረስን በመሆኑ በነዚህ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ርብርብ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን!

4ኛ. የሕዝባችንን ፍላጎት የሚያሟላ ፍትሃዊ የማኅበራዊ አገልግሎት ስርዓት ለመዘርጋት ጥራትና ተገቢነትን በሁሉም ደረጃ በማሻሻል ሁሉም ህፃናትና ወጣቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲጠቀሙ መምህራንን በማሠልጠን፣ የማስተማሪያና የመማሪያ ቁሳቁሶችን በማሟላት ጥራት ያለው ትምህርት እንዲሰጥ ማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ወሳኝ ነው፡፡ ፓርቲያችን ብልፅግና ፍትሃዊ የማኅበራዊ አገልግሎትን ለመዘርጋት ጥራትና ተገቢነት ያለው ትምህርት ለሁሉም ህፃናትና ወጣቶች ለማቅረብ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ ትግል አድርጎ በርካታ ህፃናትና ወጣቶች በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛሉ፡፡ መከላከልንና አክሞ ማዳንን መሰረት ያደረገ የማይበገር የጤና ስርአት መዘርጋት እጅግ ትኩረት የሚሻ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም መከላከልንና አክሞ ማዳንን መሰረት በማድረግ በጤናው ዘርፍም ጥራትንና ፍትሃዊነትን በጠበቀ መልኩ ለማስፋፋት እመርታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በጥልቀት ገምግመናል፡፡

ስለሆነም እኛ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ፓርቲያችን ብልፅግና በትምህርት ዘርፍ እያደረገ ያለው ከፍተኛ ርብርብና ትግል ሀገራችንን በትምህርት ዘርፍ ወደ ላቀ ከፍታ የሚወስድ፣ ተወዳዳሪና ተመራማሪ ዜጋን ከመፍጠር አኳያ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑን በማመን፤ በጤናው ዘርፍም ጤነኛና ብቁ ዜጋ ለመፍጠር መከላከልንና አክሞ ማዳን ወሳኝ የፓርቲያችን የጤና ቋሚ ምሶሶ በመሆኑ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ ከነበርንበት ጉዙ እጅግ ከፍ ባለሁኔታ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን!

5ኛ. የሀገራችንን ጥቅም እና የዜጎቻችንን ክብር የሚያስጠብቅ የውጭ ግንኙነት አቅማችንን ለማጠናከር ፓርቲያችን ብልጽግና ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲና የዲያስፖራ ተሳትፎን በማጠናከር በኩል በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ በዚህም የበርካታ ዜጎችን መብት በማስከበር ጉዳት የደረሰባቸውንም የካሳ ክፍያ እንዲያገኙ፣ የደመወዝ መከልከልና ሌሎች የመብት ጥሰጥ ለገጠማቸው ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ዜጎቻችንን ከጥቃት በመከላከል ለሀገራቸው እንዲበቁ ማድረግ ተችሏል፡፡ የዲያስፖራ ማኅበረሰብ ልማትና ሁለንተናዊ ተሳትፎን ከማሳደግ አንፃርም በተለያዩ የቴክኖሎጅ አማራጭች በመገናኘት በሀገራቸው ልማት ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን እንዲወጡ በርካታ ጥረቶች ተደርገው ውጤቶች መመዝገባቸውን ገምግመናል፡፡

በዲፕሎማሲው መስክም ሀገራችን ከጎረቤት ሀገራትና ከሌሎች ሀገሮች እንዲሁም ከዓለምአቀፍ ተቋማት ጋር የተሻለና ጥብቅ ግንኙነት በመፍጠር የሀገራችንን ጥቅም የሚያስጠብቁና በጋራ ተጠቃሚነትና በመደጋገፍ ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም እኛ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የዜጎችን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ ፓርቲያችን ብልጽግና በሚያደርጋቸው ሀገርአቀፍና ዓለምአቀፍ ጥረቶች ላይ የድርሻችንን ለመወጣትና የሀገራችንን ተፅዕኖ ፈጣሪነት ከፍ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ንቁ ተሳታፊ ለመሆንና የድርሻችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን!

6ኛ. ፓርቲያችን ብልጽግና ጥራቱን የጠበቀ ፍትሐዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ማረጋገጥ ቀዳሚ አጀንዳው በመሆኑ በመንገድ፣ በኤሌክትሪክ በቴሌኮም፣ በውኃና ሳኒቴሽን፣ በትራንስፖርትና በመስኖ መሰረተልማቶች በርካታ ውጤቶች አስመዝግቧል፡፡ እነዚህ ተግባራት የሕዝባችንን የአኗኗር ሁኔታ የሚያሻሽሉና ወደ በለፀገ ማኅበረሰብ የምናደርገውን ጉዞ የሚያፋጥኑ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ተደራሽነታቸውንም በማስፋት በርካታ የገጠር ቀበሌዎች በነዚህ የመሰረተልማት አውታሮች ተደራሽ መሆናቸውን በኮንፈረሳችን ገምግመናል፡፡ ፓርቲያችን ብልጽግና በቀሪ ጊዜያት ያቀዳቸው ሰፋፊ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታዎች፣ የቴሌኮም ማስፋፍያዎች፣ የንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦቶች፣ የመስኖ አውታሮች የሕዝባችንን ኑሮ የሚያሻሽሉና ዘመናዊነትን የሚያሳልጡ በመሆናቸው እኛ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች እነዚህ የመሰረተልማት ስርጭቶች ጥራታቸውንና ፍትሃዊነታቸውን በጠበቀ መልኩ እንዲከናወኑ የራሳችንን ኃላፊነት ለመወጣትና ኅብረተሰባችንን በማስተባበር ተጠቃሚ ለማድረግ የድርሻችንን እንወጣለን!

7ኛ. የአማራ ክልል ባለብዙ ፀጋ ባለቤትና የአፍላ ጉልበት ምንጭ በመሆኑ ፀጋዎቹን ተጠቅሞ ከራስ አልፎ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ሲያቀርብ የነበረ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ነገር ግን ክልላችን ከሰሜኑ ጦርነት ውድመትና ኪሳራ ሳያገግም በተፈጠረው የውስጥ ግጭት ለበርካታ የሠው ሕይወትና ለንብረት ውድመት ተዳርጓል፡፡ በተለይም የፅንፈኛ ቡድኑ በፈጠረው ወድመት በክልሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ተጎድቷል፤ ህፃናት ተረጋግተው እንዳይማሩ የአካልና የስነልቦና ችግር ተፈጥሮባቸዋል፡፡ የተሠሩ መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፤ አዳዲስ የመሰረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ የግብርና ግብአቶች በተለይም ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ በወቅቱ እንዳይገባ በየመንገዱ እንቅፋት እየሆነና እየዘረፈ ይገኛል፡፡ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ብሎም የስራ አጥነት እንዲጨምር በማድረግ ሕዝባችንን ለጉዳትና ለስቃይ ዳርጎታል፡፡

ስለሆነም በመከላከያ ሠራዊታችን፣ በክልላችን የጸጥታ ኃይል፣ በአመራራችንና በሠላም ወዳዱ ሕዝባችን ብርቱ ተጋድሎ አደጋው ተቀልብሶ ዛሬ ፅንፈኛው ቡድን በተራ ሽፍትነት ሲዘርፍና ሲያግት ይታያል፡፡ በመሆኑም እኛ የዚህ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ሕዝባችንን ለጉስቁልናና ለከፋ ችግር እያጋለጠ ያለውን ፅነፈኛና ዘራፊ ቡድን ከሠራዊታችንና ከመላው ሰላም ወዳድ ሕዝባችን ጋር በጋራ በመሆን በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች የሕግ የበላይነት እንዲከበር እና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሚያስችል ያላሰለሰ ጥረት ለማድረግ ቃል እንገባለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.