Fana: At a Speed of Life!

በአቃቂ ቃሊቲ የ60 ሺህ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጀመረ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24፣2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደርና ኦቪድ ግሩፕ ትብብር በአቃቂ ቃሊቲ የ60 ሺህ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሥራ ተጀመረ፡፡

በግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ዛሬ ኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞዋን የጀመረችበት ልዩ ቀን ነው ብለዋል።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ በርካታ የልማት ጉዞዎችን እየተሻገረች ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በእስካሁኑ ሂደት ቃል ገብተን ያልፈፀምነው የለም፤ ዛሬ የሚገነባው ፕሮጀክት ቃልን በተግባር የምንገልፅበት ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱን በቃላችን መሰረት ለመፈፀም ከዚህም በላይ መስራት እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ ሁሉም በጋራ መስራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ለከተማው ነዋሪ የቤት አቅርቦት መጠን እንዲጨምር በጋራ እንስራ ሲሉም ለግል ባለሀብቶችም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ለልማት የተነሱ አርሶ አደሮችም ላደረጉት ትብብር ምስጋና አቅርበው፤ ፕሮጀክቱ የልማት ተነሺዎችን ህይወት የሚቀይር እንደሆነ አረጋግጠዋል።

የኦቪድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዮናስ ታደሰ፤ አንገብጋቢ የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ድርጅታቸው በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ዜጎችን የሚጠቅም እንደሆነ ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች በስራ ዕድሉ ተጠቃሚ ከመሆን በተጨማሪ የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ዕድልም እንደሚመቻች ጠቁመዋል፡፡

በ3 ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ የተገለጸው ፕሮጀክቱ፤ በኢትዮጵያ 7ኛው ትልቁ የከተማ ፕሮጀክት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ቤቶቹ ለ300 ሺህ ያህል ዜጎች መኖሪያ እንደሚሆኑም የተነገረ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ለ250 ሺህ ዜጎች ቀጥተኛ የስራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

የሚገነባው ከተማ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን ያሟላ ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ እንደሚሆን ተመላክቷል።

በዘቢብ ተክላይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.