Fana: At a Speed of Life!

የትራንስፖርት ስምሪትና የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የትራንስፖርት ስምሪትና የነዳጅ ድጎማን በማጭበርበር ሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ የስምሪት ኃላፊዎች እና የትራንስፖርት ማኅበራት የቦርድ ሰብሳቢዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ መንግሥት ማኅበረሰቡ የትራንስፖርት እጥረት እንዳያጋጥመው ብሎ ሲያከናውን በነበረው የነዳጅ ድጎማ ሥራ ላይ÷ በተበላሹና በቆሙ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ ቁጥር የነዳጅ ድጎማ እንዲወሰድ በማድረግ፣ ያልተሸፈኑ መስመሮች እንደተሸፈኑ አስመስሎ የነዳጅ ድጎማውን ወስደው ለግል ጥቅም በማዋል እና ጨረታ በማጭበርበር የሙስና ወንጀል ድርጊት ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ናቸው፡፡

ከተጠርጣሪዎች መካከልም የአዲስ አበባ የትራንስፖርት ማኅበራት ቦርድ ሰብሳቢዎች፣ የቦርድ አባላት፣ የአምስቱም የመናኸሪያ የስምሪት ኃላፊዎችና ደላሎችን ጨምሮ 11 ግለሰቦች ይገኙበታል።

ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ያቀረባቸው የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ምርመራ ዘርፍ መርማሪ የጥርጣሬ መነሻውን ጠቅሶ ለተጨማሪ ምርመራ ማጣሪያ የ14 ቀን ጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው፤ የዋስትና መብት እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎትም ምርመራው ጅማሮ ላይ ስለሆነና ተጨማሪ ማጣሪያ ጊዜ አስፈላጊ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ ፈቅዷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.