Fana: At a Speed of Life!

ምክር ቤቱ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር አዋጅን አጸደቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡

ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 19ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥር እና አስተዳደር አዋጅን በሶስት ድምጸ ተዓቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ ያጸደቀው፡፡

የመኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ከሰው ልጆች መሰረታዊ መብቶች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው ነው ተብሏል፡፡

በምክር ቤቱ የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ምክንያታዊ እና ፍትሃዊ ያልሆኑ የቤት ኪራይ ጭማሪዎች በከተሞች እንደሚስተዋሉ አስገንዝበዋል።

እንዲሁም መንግስት የዜጎች መሰረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ኪራይ ጭማሪ በተለይ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የከተማ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እያስነሳ እና ዜጎችም ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡

የኑሮ ውድነትን ከሚያባብሱ ቁልፍ ችግሮች መካከል አንዱ የቤት ኪራይ ጭማሪ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ ችግሩን ለመፍታትና የመንግስት ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ እንደተዘጋጀ ተመላክቷል፡፡

የአዋጁ ዓላማ ግልጽና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር እንዲሁም የአከራይና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናግድ ስርዓት መዘርጋት ነውም ተብሏል፡፡

አዋጁ በውስጡ ስለ መኖሪያ ቤት ኪራይ ውል እና ዋጋ፣ የመኖሪያ ቤት ውልን ስለማቋረጥ፣ የአዋጁን አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር፣ የጥቆማ እና ቅሬታ አቀራረብ እንዲሁም ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን እንዳካተተ ተጠቅሷል፡፡

የምክር ቤት አባላት በሰጡት አስተያየትም÷ አዋጁ ችግር በመፍታት የአከራይ እና ተከራይ መብት ሚዛናዊ ሆኖ እንዲሄድ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1320/2016 ሆኖ በዛሬው እለት ጸድቋል፡፡

በየሻምበል ምህረት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.