Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል – አቶ ዑሞድ ኡጁሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዑሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ዑሞድ ኡጁሉ እና ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አቶ ዑሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት ÷ በክልሉ አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።

የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ቴንኩዌይ ጆክ በበኩላቸው ÷ ሰላም በሌለበት የፖለቲካም ሆነ የልማት ስራዎችን ለማከናወን እንደማይቻል ገልጸዋል።

አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ÷ ለተፈጠረው የጸጥታ ችግር የጋራ መፍትሄ ለመሻት ከክልሉ መንግስት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ናቸው።

አልፎ አልፎ የሚከሰተውን የጸጥታ ችግር በጋራ በመፍታት የክልሉን ሰላም ዘላቂ ማድረግ እንደሚገባ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

በውይይቱ ላይ የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አራት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንደተሳተፉ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.