Fana: At a Speed of Life!

ለ45ኛው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ልዑክ የእውቅና መርሐግብር ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰርቢያ ቤልግሬድ በተካሄደው 45ኛ የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳትፎ በድል ለተመለሰው የልዑካን ቡድን የእውቅናና የማበረታቻ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመርሐ ግብሩ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ÷የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን በመግለፅ ለቀጣይ ውድድሮች ትኩረት ተደረጎ መሰራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተለይ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከአሁኑ በቂ ዝግጅት መደረግ እንዳለበት ጠቅሰው÷ለዚህ ውድድር መሳካት ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ የሰሩ አካላትን አመስግነዋል፡፡

በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ አትሌቶችን በመወከል አትሌት ማርታ አለማየሁ እና አትሌት በሪሁ አረጋዊ ንግግር አድርገዋል፡፡

በውድድሩ የተመዘገበው ድል የተሻለ መሆኑን እና ቀጣይ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣት አበክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

የቡድኑ መሪና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ተስፋዬ አስግዶም (ዶ/ር) እና የቡድኑ ቴክኒክ መሪና የአትሌቲክስ ፌደሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተሩ አቶ አስፋው ዳኜ ስለውድድሩ ቆይታ አብራርተዋል፡፡

ፌዴሬስኑ ለልዑካን ቡድኑ በመመሪያው እና በአሰራሩ መሰረት የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት እንዳበረከተም የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

የልዑካን ቡድኑ በፈረንጆቹ 30 ቀን 2024 በተካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተካፍሎ በሁለት ወርቅ ፣ በስድስት ብር እና በሁለት ነሃስ በአጠቃላይ በ10 ሜዳሊያ ከዓለም የሁለተኛነት ደረጃ በመያዝ በድል ተመልሷል፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.