Fana: At a Speed of Life!

መጋቢት 24 የኢትዮጵያውያን የነጻነትና የዕኩልነት ሃዉልት የቆመበት ታሪካዊ ቀን ነዉ – አቶ ፍቃዱ ተሰማ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መጋቢት 24 የኢትዮጵያውያን የነጻነት እና የዕኩልነት ሃዉልት የቆመበት ታሪካዊ ቀን ነዉ ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ፥ በዛሬዉ ዕለት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖችና ከተሞች ‘ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ለውጡን እናጸናለን” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደዉ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተሳተፉችሁ አካላትን በሙሉ አመሰግናለሁ ብለዋል፡፡

የክልሉ ህዝብ የብልጽግና ጉዞ የተጀመረበትን ይህንን ታሪካዊ ቀን ለማሰብ የድጋፍ ሰልፍ ባካሄደበት ወቅትም የለዉጡ ዋና ኢንጂነር እና የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ለሆኑት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያለዉን አጋርነት ገልጿልም ብለዋል፡፡

ለዉጡን የሚደግፉና የሚያጠናክሩ የተለያዩ መልዕክቶችን በማሰማት እስካሁን ለተገኙት አመርቂ ድሎች እዉቅና መሰጠቱንም አድንቀዋል፡፡

መጋቢት 24 ኢትዮጵያ ከመበተን ስጋት ተላቃ ከፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስብራቶች የዳነችበት እንዲሁም በህብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትና አንድነት ሁለንተናዊ ለዉጥ መረጋገጥ የጀመረበት ቀን በመሆኑ ዕለቱ በሀገሪቱ ታሪክ ዉስጥ የተለየ ስፍራ እንደሚሰጠውም ነው የተናገሩት ሃላፊው፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ለተሳተፉ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳና ሃደ ሲንቄዎች፣ ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የድጋፍ ሰልፉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የሰላም ዘብ ለሆኑ የጸጥታ አካላት፣ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችና በየደረጃዉ ለሚገኙ አመራሮችም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

”በፓለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተጎናጸፍናቸዉን ድሎች በመንከባከብ፤ የገጠሙንን ሀገራዊ ፈተናዎች በጽናት በመሻገር በላቀ ድል የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እንደ ትላንቱ ሁሉ ዛሬም በትብብርና በጋራ እንጓዝ” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አክለውም ፥ ”መጋቢት 24 የኢትዮጵያዊያን የነጻነት እና የዕኩልነት ሃዉልት የቆመበት ታሪካዊ ቀን ነዉ” ማለታቸውን የዘገበው ኦቢኤን ነው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.