Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ መንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግብ ማሳካትን እንደግዴታ ወስዶ እየተገበረ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል መንግስት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግብ ማሳካትን እንደ ምርጫ ሳይሆን እንደ ግዴታ ወስዶ በመተግበር ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በማበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ እንዳሉት፥ ኢትዮጵያ ከ“ዲጂታል ኢትዮጵያ” ኢኒሼቲቭ የመነጨ የ“2025 ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን” እቅድ ቀርፃ በመተግበር ላይ ትገኛለች።

የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ” ኢኒሼቲቭ ሁሌም የአዳዲስ አሳቦች ባለቤት በሆኑት የዓለም የሰላም ሎሬት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመነጨ ነው ብለዋል።

የዲጂታል ትግበራ ከሁሉ በላይ በከተማ ልማት ረገድ የተያዙትን ግቦች በማሳካት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑ ታምኖ በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ እንደሚገኝም አንስተዋል አቶ ሽመልስ።

የከተማ የዲጂታል ትግበራ በርካታ ማዕቀፎች ያሉት ቢሆንም ዋነኛው “ስማርት” ከተማን መገንባት እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ይህም በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ፣ የመንግስት አገልግሎትን ጥራት ማሻሻል፣ የስራ አፈፃፀም ብቃትን ማሳደግ፣ መረጃን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ እና የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ናቸው ብለዋል።

በዚህ ረገድ፣ በተወሰኑ ከተሞች የተለየ የዲጂታላይዜሽን ትግበራ መጀመሩንም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል፡፡

አክለው እንዳሉትም፥ ትግበራው የአገልግሎት ጥራት ችግር የሚስተዋልባቸው ዘርፎች የመሬት አስተዳደር፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ኢንቨስትመንትና ኮንስትራክሽን ዘርፎች ውስጥ የሚስተዋለውን የአገልግሎት ችግር 50 በመቶ መቀነስ ግብ አድርጎ በመተግበር ላይ ነው።

በአዳማ ከተማ የሰነዶች ዲጂታላይዜሽን ስራ ከ90 በመቶ በላይ እንዲሁም አጠቃላይ አገልግሎት 70 በመቶ መድረሳቸውን እንደአብነት ያነሱት ነው።

በተጨማሪም በከተማዋ የዜጎችን ደህንነት በማረጋገጥና የትራፊክ ፍሰትን በማሻሻል ረገድ አበረታች ለውጥ እያስመዘገበ እንደሆነ ያነሱት አቶ ሽመልስ፥ ክልሉ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግብ ማሳካትን እንደ ምርጫ ሳይሆን እንደ ግዴታ ወስዶ በመተግበር ላይ ይገኛል ብለዋል።

ወደ ዲጂታል ትግበራ በገቡት ከተሞች የታየው የአፈፃፀም ሁኔታ ሲገመገም፣ የዘርፎቹን አጠቃላይ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ወደ “ኦንላይን”ለማምጣት የተያዘው እቅድ የሚሳካ መሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑንም ነው የጠቀሱት።

በዚህ ረገድ የተያዘውን ግብ ለማሳካት፣ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ዝግጁነት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ክልሉ ለዚህ እቅድ ስኬት ለማበርከት ፍላጎት ካላቸው ከማንኛውም አካላት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.