Fana: At a Speed of Life!

ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ስኬት ስፔን ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የያዘችው ዕቅድ እንዲሳካ ስፔን የምታደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር ጉይሌርሞ አንቶኒዮ ሎፔዝ ማክሊላን አረጋገጡ፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከአምባሳደሩ እና ከስፓኒሽ ኮርፖሬሽን ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ በስፔን መንግሥት የሚደገፈው የስፓኒሽ ኮርፖሬሽን በጤናው ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡

የስፓኒሽ ኮርፖሬሽን በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን እና ለዚህም ምሥጋና እንደሚገባው ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡

አምባሳደሩ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ አገልግሎት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በተለያዩ የጤና እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሚኒስቴሩ ጋር በትብብር በመሥራታችን በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል ብለዋል፡፡

የስፔን መንግሥትም ለኢትዮጵያ ጤና ዘርፍ ከሚያደርገው ድጋፍ ውስጥ÷ 90 በመቶው በግጭት የተጎዱ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እንደሚውል መናገራቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በጤናው ዘርፍ የሰው ኃይልን ለማሰልጠን፣ የእናቶች እና የሴቶች ጤናን ለማጎልበት እንዲሁም ከዓየር ለውጥ ጋር በተያያዘ እየተሠሩ ላሉ እና ለሚሠሩ ሥራዎች ቅድሚያ እንደሚሰጡም አስታውቀዋል፡፡

ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ዕቅድ ስኬት ስፔን የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.