Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመጪው ክረምት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ም/ሃላፊ አቶ ኤሊያስ ከድር ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት÷ ባለፉት አምስት ዓመታት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቃሜታ ያላቸው 18 ነጥብ 6 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።

የተተከሉት ችግኞች የጽድቀት ምጣኔም 88 ነጥብ 5 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል፡፡፡

ለ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በክልሉ ሁሉም ዞኖች 5 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ የማፍላት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን በተከናወነ ሥራ 94 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆነው ችግኝ ለቆጠራ መድረሱን የጠቀሱት ም/ሃላፊው÷ ከዝግጅቱ ጎን ለጎንም የመትከያ ቦታ የማዘጋጀት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም አሁን ላይ 1 ነጥብ 29 ሚሊየን ሄክታር መሬት የችግኝ መትከያ ቦታ መለየቱን ገልጸዋል፡፡

ቀድም ሲል ከተከናወነው የተፋሰስ ልማት ሥራ ጎን ለጎን የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ መከናወኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ዘንድሮ በክልሉ እየተዘጋጁ ከሚገኙት ችግኞች መካከል 11 በመቶ የሚሆኑት የፍራፍሬ እና ቀርከሃ ዝርያዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.