Fana: At a Speed of Life!

መገናኛ ብዙሃን ሀገራዊ ጥቅምንና አንድነትን በማጠናከር በኩል ሁለገብ ኃላፊነት አለበት ተባለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መገናኛ ብዙሀን ሀገራዊ ጥቅምን በማስጠበቅና የዜጎችን አንድነት በማጠናከር በኩል ሁለገብ ኃላፊነት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በብሄራዊ ጥቅምና ሙያዊ ጋዜጠኝነት ዙሪያ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

በስልጠናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ÷ መገናኛ ብዙሃን ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ተጨባጭ እና ትክክለኛ መረጃ በማቅረብ ሀገራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ረገድ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመረዳት የሀገር ጥቅምን በሚያስጠብቁ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩም አመልክተዋል።

የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር ባድሩ በበኩላቸው÷ መገናኛ ብዙሃን ለውጭ ፖሊሲ ስኬት ቁልፍ መሳሪያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚነገሩ ሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳዎችን በመመከት ሚዛናዊና እውነተኛ ዘገባዎችን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማቅረብ ከመገናኛ ብዙሃኑ እንደሚጠበቅ ገልጸው፤ በዚህ ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።

የመንግስት ኮሙኒኬሽ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ÷ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ስትራቴጂና የውጭ ፖሊሲ መሰረት በማድረግ የሀገር ግንባታ ስራዎችን መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡

ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በማጠናከር የጸጥታና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር የሀገሪቱን ስም የሚገነቡ ሪፖርቶች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸውም ተብሏል፡፡

በሲፈን መገርሳ እና ገመቺስ ታሪኩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.