Fana: At a Speed of Life!

በአማራ ክልል ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በሰብል ለማልማት የእርሻ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በ2016/2017 የምርት ዘመን ከ5 ነጥብ 1ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብል ለማልማት የተጠናከረ የእርሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

“ያለግብርና የለም ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ የ2016/2017 የምርት ዘመን የሰብል ልማት የንቅናቄ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ የግብርና ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው እንዳሉት÷ በመጪው የምርት ዘመን ለሚከናወነው የሰብል ልማት እንቅስቃሴ ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በምርት ዘመኑ ከ5 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት የእርሻ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና ከዚህም 169 ሚሊየን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግም ማዳበሪያ ቀደም ብሎ መቅረብ መጀመሩን ጠቅሰው÷ለኢንዱስትሪ ግብዓት፣ ለውጭ ገበያ የሚውልና የምግብ ሰብል በስፋት እንደሚመረት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የክልሉን የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በመጪው የመኸር ወቅት ሰላምን ከማስጠበቅ ጎን ለጎን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው የሚገኘው የግብርና አመራር አባላትና ባለሙያ፣ እንዲሁም አጋር አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.